መገናኛ ብዙሃንና የሃይማኖት ተቋማት ህዝብን የማቀራረብ ስራ ላይ ማተኮር አለባቸው

143

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ)  መገናኛ ብዙሃንና የሃይማኖት ተቋማት ህዝብን የማቀራረብ ስራ ላይ በማተኮር አብሮነትን፣ ሰላምንና አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ።

በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት አድርገው የሚነሱ ግጭቶችን ማስቆምና የመፍትሄው አካል በመሆን መስራት ይገባልም ተብሏል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችና የሚዲያ ሃላፊዎች እንደገለጹት ለበርካታ ዓመታት ዘርንና ማንነትን መሰረት አድርጎ ሲሰራበት የነበረው የፖለቲካ አካሄድ አሁን እየተከሰተ ላለው ችግር ዋነኛ ምክንያት ሆኗል።

በመሆኑም ይህንን የቆየ ችግር ለመፍታት እንዲቻል በተለይ የሃይማኖት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃኑ በአገሪቱ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመተንተን መፍትሄ ለመሻት መስራት ይጠበቅባቸዋልም ነው ያሉት።

የኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ (ኦ ቢ ኤን) ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናቡ አስራት''ላለፉት ጊዜያት ህብረተሰብን የማገናኘት ሥራዎች አልተሰሩም፤ የማራራቅ ሥራ ነበር የተሰራው'' ብለዋል።

ባለፉት 30 ዓመታት ብሄርን ከብሄር የማጋጨትና የኢትዮጵያን እሴት የሚያበላሹ፤ የነበረን እሴት የሚጎዱ ነገሮች ተሰርተዋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ በበኩላቸው ጥላቻን በመንዛት የፖለቲካ ልዩነትን በማስፋት፤የብሔሮችን ግጭት እና የእምነት ተቋማትን የማለያየት ስራ ሲሰራ ነበር ብለዋል።

ዶክተር ሙላቱ ''ይህ ሰላምን ከማምጣት ይልቅ ግጭትን የሚያባብስ'' ተግባር እንደነበር ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የተገኙት ዶክተር አቡነ አረጋዊ ህዝቡ ወደ ነበረበት የአብሮነት ስሜት እንዲመለስና አንድነቱን አጠናክሮ በኢትዮጵያዊነት ባህልና ስርዓት መተሳሰብ፣ መከባበር፣ መረዳዳት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ''ሁላችንም ትኩረት ሰጥተን የሚዲያ አካላትም የሃይማኖት ተቋማትም መስራት ይጠበቅብናል'' ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻድቁ አብዶ በሃይማኖት ውስጥም ግጭቶች የተከሰቱባቸው አካባቢዎች እንደነበሩ ተናግረዋል።

ግጭት ከእምነቱ አስተምህሮ የማይጠበቅ ነው ያሉት ፓስተሩ ''ሌላ ሰው እጅ ላይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ የኔ አስተዋጽኦ በዚህ ጉዳይ ምንድነው ብለን እያንዳንዳችን ራሳችንን መርምረን ከዚህ አይነቱ መንገድ መመለስ አለብን'' ብለዋል።

በየቦታው የሚፈነዱ የምናያቸው ግጭቶች ተፈጥሯቸው የተወለዱት በብሔር ፖለቲካ አጥር ውስጥ ብሔርተኝነት ወይም በጠነከረ ዘረኝነት ውስጥ የተሰራች ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ነበረች'' ያሉት ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ናቸው።

ጋዜጠኛ ጥበቡ ''ይሄ የተሰራችበት መዋቅር መፍረስ ሲጀምር ነው ያበጡት ግጭቶቹ በየቦታው እየፈነዱ የመጡት'' ብለዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ጥቃቶች ማብቂያ ሊበጅላቸው እንደሚገባ የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መደገፍና ማጽናናት የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ታላቅ አገር በመሆኗ ከውስጥም ከውጭም የሚቃጡባትን ጥቃቶች እየመከተች ዛሬ ላይ መድረሷን አስታውሰው፣ በአገሪቷ ሰላም እንዳይኖር የሚሰሩ አካላትን በጋራ መመከት አለብን ብለዋል።

በተለይ የሃይማኖት ተቋማትና መገናኛ ብዙሃን አገርና ህዝብ የማገልገል ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

መንግስትም በወንጀል መጠየቅ የሚገባቸውን ግለሰቦችም ይሁን ቡድኖች ህግ ፊት ማቅረብና ተጠያቂ ማድረግ አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም