ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የሚተላለፉ ተቋማት ተጠያቂ ይሆናሉ - የጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የሚተላለፉ ተቋማት ተጠያቂ ይሆናሉ - የጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ የሚተላለፉ ተቋማት ተጠያቂ እንደሚሆኑ የጤና ሚኒስቴር አሳሰበ።
የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19ን ወረርሽኝን ለመከላከል ከጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን አገር አቀፍ የንቅናቄ መርሃ ግብር ያስጀምራል።
የጤና ሚኒስቴር ንቅናቄውን ስኬታማ ለማድረግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በሚኖረው ሚናና ኃላፊነት ላይ ዛሬ ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ በንቅናቄው አማካኝነት ሰዎች በብዛት በሚሰበሰቡባቸው ሥፍራዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ተግባራዊ እንደሚሆንም ተገልጿል።
ኅብረተሰቡ ስለ ወረርሽኙ ያለውን ግንዛቤ እንዲያጎለብት የማስተማር ሥራ እንደሚሰራም ነው የተጠቆመው።
በተጨማሪ ጭንብልና የእጅ መታጠቢያን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ ህብረተሰቡ የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ረገድ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚሰጥም ተመላክቷል።
የምክር ቤት አባላት በዚህ ወቅት የቫይረሱን ስርጭት በሚመለከት ያሉት መዘናጋቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

በተለይ ህዝብ በብዛት የሚገለገልባቸው የመንግሥትና የግል ተቋማት ላይ የሚታየው ቸልተኝነት ወረርሽኙን እንደሚያባብሰው ስጋታቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪ በክልሎችም መሰል መዘናጋቶች በስፋት እየተስተዋሉ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለንቅናቄው ውጤታማነት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የተነሱት ሃሳቦች ትክክልና መቀየር ያለባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩም በቅርቡ በሚጀምረው የንቅናቄ መርሃ ግብር ኅብረተሰቡን ዳግም የማንቃትና ግንዛቤውን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥትና የግል ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
መመሪያውን ተግባራዊ የማያደርጉ ተቋማት ተጠያቂ እንደሚሆኑ አስጠንቅቀው፣ ለተግባራዊነቱም ከሰላም ሚኒስቴርና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች ተቋማት እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ምክር ቤቱ ክትትል እንዲያደርግም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጥሪ አቅርበዋል ።
ንቅናቄው የታለመትን ዓላማ እውን እንዲያደርግ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዳለበትም ነው የተናገሩት።
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ከ126 ሺህ በላይ አልፏል፤ በቫይረሱም ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ከ1ሺህ 900 በላይ ሆኗል።