በእሳት አደጋ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት ወደመ -ፖሊስ

121

ጅማ፣ ታህሳስ 30/2013 (ኢዜአ) በጅማ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማው ፖሊስ መምሪያ የወረዳ ሁለት ጽህፈት ቤት ዋና አዛዥ ኮማንደር ካሊድ አባ ተማም ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ንጋት አካባቢ 11 ሰዓት ከ30 ደቂቃ ላይ ነው።

በከተማው በቦቾ ቦሬ ቀበሌ መናኸሪያ አካባቢ በሚገኝ በሚገኝ አንድ  የእንጨት ስራ ወጤቶች ማምረቻና መሸጫ የግል ድርጅት ላይ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል።

በአደጋው በድርጅቱ ተመርተው ለገበያ የተዘጋጁ ዘመናዊ የእንጨት ስራ ውጤቶች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን አመልክተዋል።

"የወደመው ንብረት 6 ሚሊዮን ብር ግምት አለው" ያሉት ኮማንደር ካሊድ በአደጋው በሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

በአካባቢው ነዋሪዎች፣ በጸጥታ አካላትና በእሳት አደጋ መከላከያ ሰራተኞች ትብብር በተደረገ ጥረት ቃጠሎው ወደ ሌሎች የንግድ ተቋማት ሳይዛመት በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

እንደ ኮማንደር ካሊድ ገለጻ የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም