ከመተከል ዞን ለተፈናቀሉ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ ተደረገ

ደብረ ማርቆስ፣ ታህሳስ 30/2013( ኢዜአ) በመተከል ዞን በተከሰተ ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል ድጋፍ መደረጉን የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጽህፈት ቤቱ ኅላፊ አቶ የኔነህ ሁነኛው ለኢዜአ እንደገለጹት ለተፈናቃዮቹ የተደረገው የምግብ እህል ድጋፍ በዞኑ ስር ከሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተሰበሰበ ነው።

ድጋፉ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በተከሰተ ግጭት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ለተፈናቀሉ ወገኖች ጥቅም ላይ የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ከዞኑ ነዋሪዎች የተሰበሰበ ከ450 ኩንታል በላይ ስንዴ፣ ጤፍ፣ የበሶ ዱቄትና ሌሎች የእህል አይነቶች ተፈናቃዮች ወደ ሰፈሩበት አካባቢ መላኩን ተናግረዋል።

ተፈናቃዮች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የዞኑን ህዝብ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

ለተፈናቃዮች ድጋፍ ለማሰባሰብ በተከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ከ100ሽህ ብር በላይ መሰብሰቡንም አመልክተዋል።

የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታነህ ሁንዴ "ከሶስት ጓደኞቼ ጋር በመሆን አንድ ኩንታል ዱቄት ገዝተን ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲውል አስረክበናል" ብለዋል።

"መረዳዳት ኢትዮጵያዊ ባህላችን በመሆኑ በቀጣይም ሰርቼ ከማገኘው ገንዘብ በመቀነስ የጀመርኩትን ድጋፍ አጠናክሬ እቀጥላለሁ"ሲሉም ተናግረዋል።

"አንድ ኩንታል የስንዴ ዱቄትና ሀምሳ ኪሎ ጨው ገዝቼ  ለተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲውል ለአስተባባሪዎች አስረክቤያለሁ" ያሉት ደግሞ የደጀን ከተማ ነዋሪ አቶ ላመስግን ቢሆነኝ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም