በመተከል ዞን የገና በዓልን በሰላምና አብሮነት አክብረናል- የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች

83

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ የገና በዓልን በሰላምና አብሮነት ማክበራቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። 

የሀገር መከላከያ ሰራዊት የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ ላበረከተው አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በመተከል ዞን 'የተደራጁ ሽፍቶች' በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

በተጨማሪም ህግ-ወጥ ቡድኑ ዜጎች ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረት አውድሟል።

የዞኑን የጸጥታ ሁኔታ የሚመራ ግብረ ሃይል በፌደራል መንግስት ተቋቁሞ የህግ ማስከበር ስራ እያከናወነ ሲሆን፤ አሁን ላይ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ ተገልጿል።

ይህም በመሆኑ የግልገል በለስ ከተማ ነዋሪዎች የገና በዓልን በከተማዋ የሚኖሩ ሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በአብሮነትና በመደጋገፍ ማክበራቸውን ገልጸዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአጭር ጊዜ ውስጥ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም በማስፈን ረገድ ላበረከተው አስተዋጽኦም ነዋሪዎቹ ምስጋና አቅርበዋል።

የአካባቢው ህብረተሰብ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዞኑ በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ተጋብተውና ተዋልደው በአብሮነት እንደሚኖሩ አስታውሰው፤ ሁሉም የዞኑ ነዋሪዎች ይህን አብሮነት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ነዋሪዎቹ ጥሪ አቅርበዋል።

የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት መፍታት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የዞኑን ሰላም ለማስጠበቅ በፌደራል መንግስት የተቋቋመው ግብረ-ሃይል ህግ ከማስከበር ስራ ጎን ለጎን ህዝባዊ ውይይቶችን እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም