የመተከል ግጭት የህዳሴ ግድብን ለማስተጓጎል የታለመ መሆኑን በመገንዘብ ለመፍትሄው ሊሰራ እንደሚገባ ተመለከተ

2038

አሶሳ፣ ታህሳስ 30 / 2013(ኢዜአ) በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚፈጠረው ግጭት የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማስተጓጎል ያለመ መሆኑን የክልሉ ህዝብ በሚገባ ተገንዝቦ ለመፍትሔው ሊሠራ እንደሚገባ ተመለከተ። 

በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና ሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሃገር ሽማግሌዎች ጋር በአሶሳ ተወያይተዋል፡፡

የሃገር ሽማግሌዎች ተወካይ ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ በወቅቱ እንዳሉት ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኢትዮጵያውን አሻራ ያረፈበት የህዳሴው ግድብ መገኛ ነው፡፡

ክልሉ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ማብሰሪያ ነው፤ በአካባቢው ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረግበትም ምክንያት ይኸው ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ቢደናቀፍ የመጀመሪያ ተጎጂ የቅርብ ተጠቃሚ የሆነው የክልሉ ህዝብ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሃገር ሽማግሌዎች በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች ሲዘዋወሩ በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቱ ዘላቂ መፍትሔ እንዲኖረው አመራሮች በሃላፊነት እንዲሠሩ ጥያቄ እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል፡፡

ሁሉም አመራር የሚመራውን ህዝብ ደህንነት መጠበቅና መገናኛ ብዙሃንም ግጭትን ከማራገብ ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ እና የሃገር ሽማግሌዎች ጥምረት ምክትል ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በበኩላቸው ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በህዳሴው ግድብ ምክንያት የዓለምን ትኩረት ስቧል ብለዋል፡፡

ክልሉ በሚቀጥሉት አስር  ዓመታት ውስጥ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ እንደሚሆን እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በክልሉ ትምህርት እና መሠረተ ልማት በሚገባ ያላገኙ ነዋሪዎችንም ህይወት ይቀይራል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ኀብረተሰቡ በክልሉ ተደጋጋሚ ግጭት እንዲነሳ የሚደረገው የልማቱ ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ለማድረግ እንደሆነ መረዳት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

አልከድር አህመድ የተባሉ የክልሉ ሃገር ሽማግሌ እንደ ክልል ብቻ ሳይሆን እንደሃገር የገጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች፣ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት እና መንግስት የሚጠበቅባቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት እንዳሉት ክልሉ በሚጠበቅበት ደረጃ አለመልማት ለጸረ ሠላም ሃይሎች ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

ህገወጥ የጦር መሳሪያንም መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ ለወጣቱ ስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃንም ግጭት ማራገብ ሳይሆን ሰብዓዊነት በተሞላበት መልኩ እንዲዘግቡና ጥምረቱ ለመፍትሄው  መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

በክልሉ በቆዳ ቀለም ልዩነት ምክንያት የሚፈጸም ሞት መቅረት አለበት ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ጸሎቴ ትግሬ የተባሉ የውይይቱ ተሳታፊ ናቸው፡፡

ለግጭቱ  ምክንያት የሆኑ  ለህግ እንዲቀርቡ ከመንግስት ፣ሃገር ሽማግሌ እና ሃይማት ተቋማት ጉባኤ ጥምረት ጎን ቆመን እንሠራለን ሲሉም አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ የበላይ ጠባቂ ተቀዳሚ ሙፍቱ ሃጂ ኡመር የሰው ልጅ በሰውነቱ ሊከበር ይገባል ብለዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ስለመተከል ግጭት ግንዛቤ ማግኘታቸውን የተናገሩት ሙፍቱ ሃጂ ኡመር ፤ መንግስት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለችግሩ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ እንሠራለን ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሃገራችን በብዙ ፈተና ውስጥ ናት ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ጉባኤ እና የሃገር ሽማግሌዎች መማክርት ጥምረት ሰብሳቢ ብጹዕ አቡነ ጎርጎሪዮስ ናቸው፡፡

በሃገሪቱ ሞት እና ስደት እንዲበቃ ሁላችንም በአንድ ሃሳብ መስራት አለብን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው ኮማንድ ፖስት  መተከልን ተረክቦ ከተቆጣጠረ ወዲህ  የዞኑ ሠላም እየተረጋጋ መሆኑንና ይህን ተከትሎ ህብረተሰቡ በአካባቢው የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ ያለስጋት ለጸጥታ ሃይሉ ጥቆማ መስጠት መጀመሩን  ኢዜአ ቀደም ብሎ ዘግቧል፡፡