ቦይንግ ኩባንያ ተከስክሰው ከነበሩት ሁለት የ737 ማክስ አውሮፕላኖች ጋር ተያይዞ ለቀረበበት ክስ 2.5 ቢሊዮን ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማማ

651

ታህሳስ 30/2013 ( ኢዜአ)  ቦይንግ ኩባንያ ተከስክሰው በነበሩት የኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ጋር ተያይዞ ለቀረበበት ክስ ለአየር መንገዶቹ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች 2.5 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ካሳ ለመክፈል ተስማምቷል።

እንደ ቢ ቢ ሲ ዘገባ ለአውሮፕላኖቹ መከስከስ በምክንያትነት ቦይንግ በአውሮፕላኖቹ ላይ የተገጠሙትን የደህንነት መቆጣጠሪያ መረጃዎች በተገቢው ሁኔታ ለአብራሪዎችና ቴክኒሽያኖች ግልጽ አለማድረጉ መሆኑን የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ አረጋግጧል፡፡

በተከሰተው ችግር በካሳ ክፍያ ከተወሰነው ገንዘብ ውስጥ 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላሩ በቀጥታ በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ የ346 ተጎጂ ቤተሰቦች የሚከፈል መሆኑም ተገልጿል፡፡

እንዲሁም አብዛኛው የካሳ ክፍያ የሆነው 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላሩ በአየር መንገዶቹ በረራ ማቆም ጉዳት ለደረሰባቸው የኢትዮጵያው እና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች የሚከፈል ነው ተብሏል።

ግዙፉ የቦይንግ ኩባንያ ከዚሁ ከአውሮፕላኖቹ የደህንነት መጓደል ክስ ጋር በተያያዘ ለፈጸማቸው ጥፋቶች 243 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ይቀጣል ነው የተባለው።

ድርጅቱ ይህን ካሳ ለተጎጂ ቤተሰቦች ለመክፈል የተስማማ መሆኑን የድርጅቱ ሀላፊ ዴቪድ ካልሆን መግለጻቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሀላፊው አክለውም “እንዲህ አይነት ትክክለኛ ውሳኔ ላይ መድረሳችን ለድርጅታችን ተዓማኒነት መጨመር ትልቅ ዋጋ አለው” ሲሉ መናገራቸውንም የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል፡፡

ሀላፊው አክለውም “ይህ ክስተትና ውሳኔ እንደ ድርጅት ለሁሉም አብራሪዎችና ተቆጣጣሪዎች በምን ያህል መጠን ግልጽ መሆን ያለብንና ግዴታችንም ከፍተኛ መሆኑን በማስታወስ በኩል ትልቅ ሚና ያለው ነው ማለታቸውም ተገልጿል፡፡

የምርመራ ውጤቱ የሚያሳየው የአብራሪዎች ማሰልጠኛ ማኑዋሉ የአውሮፕላኑን ሲስተም፣ ከማኮብኮቢያ ስፍራ ሲነሱ እና በበረራ ወቅት ችግር ሲገጥማቸው ምን ማድረግ እንደሚገባቸው በተገቢው መንገድ መረጃ መስጠት ላይ ክፍተት እንዳለበት የሚያመላክት መሆኑን የአሜሪካ ፍትህ ቢሮ መግለጹም በዘገባው ተመልክቷል፡፡

ቢሮው አክሎም የአደጋውን መንስኤ ለመመርመር በተደረገው የምርመራ ሂደት ላይ ቦይንግ ላለፉት 6 ወራት ምንም አይነት ትብብር እንዳላደረገ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡