በመተከል ዞን የማንቡክ ከተማ ነዋሪዎች በመተከል ዞን ህግ በማስከበር ስራ ላይ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል አባላት ሰንጋዎችን አበረከቱ

107

ታህሳስ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የማንቡክ ከተማ ነዋሪዎች በዞኑ ህግ በማስከበር ስራ ላይ ለሚገኘው የፀጥታ ሃይል አባላት ለገና በዓል 210 ሺህ ብር ወጪ የተደረገባቸው ስድስት የእርድ ሰንጋዎችን አበረከቱ።

በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው ግብረ ሃይል በመተከል ዞን ፀረ ሰላም ሃይሎችን በማደንና በአካባቢው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል።

ግብረ ሃይሉ ከዞን እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር በተንኮልና ሴራ ውስጥ የገቡ አመራሮችን የማጥራት፣ ህዝባዊ አንድነትን የማጠናከርና ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን የመፍታት ስራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በአካባቢው በዜጎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ሽፍቶችን በማደን ለህግ የማቅረብ ስራም በማከናወን ላይ ነው።ግብረ ሃይሉ ባከናወነው ተግባር በርካታ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ሰላማቸው እየተመለሱ ሲሆን ህዝባዊ የውይይት መድረኮችም በመካሄድ ላይ ናቸው።

በዚህም ደስተኞች ነን ሲሉ ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ በዞኑ ዳንጉር ወረዳ የማንቡክ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ ለፀጥታ ሃይሉ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት የበዓል መዋያውን ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

ግብረ ሃይሉ በአካባቢው ስላመጣው አንፃራዊ ሰላም ደስተኞች መሆናቸውን የገለጹት ነዋሪዎቹ፤ ድጋፋቸው እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዳንጉር ወረዳ ህዝቡ ባደረገው ውይይት ህዝብን ከህዝብ የማጋጨትና ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲፈጸም ያደረጉ አካላት ተለይተው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ ማንኛውንም በዓል በጋራ የማክበርና የአብሮነት ልምድ እንዳለው የገለጹት የአካባቢቅው ሽማግሌዎች "የገና በዓልን በለመድነው አብሮነት እያከበርን ነው" ብለዋል።

ማህበረሰቡ የለገሰውን ስጦታ የተረከቡት ሻለቃ ፍቃዱ ጃፍራ ለተደረገው ድጋፍ ሁሉ በሰራዊቱ ስም አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም