ሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ እና የደብረብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችን አስመረቁ

84
መቀሌ ደብረብርሃን ሐምሌ 15/2010 ሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ መቀሌ ካምፓስ እና የደብረብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ያሰለጠኗቸውን 420 ተማሪዎችን አስመረቁ፡፡ በሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ የመቀሌ ካምፓስ ዲን አቶ ዳዊት ንጉስ ዛሬ በተካሄደው የምረቃ ስነስርዓት ወቅት እንደገለጹት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በመደበኛና በማታ ፕሮግራም ካስመረቋቸው 222 ተማሪዎች ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ ሴቶች ናቸው። ተመራቂዎቹ ከሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች መካከል አካውንቲንግና ቢዝነስ ማናጅመንት ይገኙበታል። የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ደሪብሳ ዱፌራ ተመራቂዎች  በሰጠለኑበት የሙያ መስኮቸ ህዝብን ለማገልገል ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። ተቋሙ መንግስትን በመደገፍ  የትምህርት ሽፋን ለማዳረስ እየተደረገ ያለውን ጥረት በጥራትም ላይ ለመድገም በሚያካሄደው እንቅስቃሴ  መምሀራን የላቀ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ደሪብሳ እንዳሉት ሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ ከምፓሶቹን ከ39 ወደ 50 ለማሳደግ ፈቃድ አግኝቶ እየሰራ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው በሂሳብ ስራ የዲግሪ ተመራቂ ተማሪ ፍትግ ኃይሌ በሰለጠንችበት ሙያ ከቤተሰብ ጠባቂነት በመውጣት ሰርታ ራሷንና ቤተሰቧን  ብሎም  ህብረተሰቡን ለመርዳት መዘጋጀቷን ተናግራለች፡፡ የቢዝነስ ማናጅመንት ተመራቂ ገብረአነንያ ገብረእግዜአብሔር በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል ህብረተሰቡን ለማገልገል ጥረት እንደሚያደርግ ገልጿል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የደብረብርሃን ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጤና አክስቴንሽንና አዋላጅ ነርስ በአጠቃላይ በደረጃ ሶስትና አራት ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከል ሙላቱ ዳኜ በሰጠው አስተያየት በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ የህብረተሰቡን የጤና ችግር ለመፍታት የድርሻውን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡ መንግስት በሚመድባት ቦታ ሁሉ ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነተ ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን የገለጸችው ደግሞ የአዋላጅ ነርስ ተመራቂዋ ስንታየሁ ጌቴ ናት። የኮሌጁ ዲን አቶ ማሙየ መንገሻ  በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንዳመለከቱት ኮሌጁ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ስራ በተጓዳኝ በክልሉ እና ከክልሉ ዉጪ በመንግስት ተመድበው ለሚመጡ የጤና ባለሙያዎች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ከዘንድሮ ተመራቂዎቹ መካከል 144 ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኮሌጁ  እስካሁን ከአምስት ሺህ በላይ መካከለኛ የጤና ባለሙያዎችን ማሰልጠኑም ተመልክቷል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም