የዘንድሮው የታላቁ ሩጫ ውድድር የኮቪድ-19 መከላከል መመሪያን ተከትሎ ይከናወናል

69

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 28/2013(ኢዜአ)የዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የኮቪድ-19 ወረረሽኝን ለመቆጣጠር የወጡ መመሪያዎችን ተከትሎ ይካሄዳል።

20ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ በዘንድሮው ውድድር 50 ሺህ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል።

ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በወጡ መመሪያዎች መሰረት ታቅዶ ከነበረው የውድድሩ ተሳታፊ 25 በመቶው ብቻ እንሚካፈሉና በዚሁ መሰረት 12 ሺህ 500 ሰዎች በውድድሩ ላይ ይካፈላሉ ብለዋል።

የውድድሩ ተሳታፊዎች ምዝገባውን በኤሌክትሮኒክስ የግብይት አማራጭ እንዲፈጽሙ መደረጉንና ይሄም የአካል ምዝገባን እንዳስቀረ ተናግረዋል።

አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የመወዳደሪያ ቲሸርቶችን በማዘጋጀት ተሳታፊዎች እንደሚለብሱት የቲሸርት ቀለም አይነት በሂልተን፣ ቦሌና መገናኛ አድርገው ወደ ውድድሩ ስፍራ እንደሚመጡ ይደረጋልም ነው ያሉት አቶ ኤርሚያስ።

ማህበሩ ለተሳታፊዎች የአፍና አፍንጫ ጭምብል ያዘጋጀ ሲሆን ጭምብሉን ያላደረገ ተሳታፊ ወደ ውድድሩ ቦታ መግባት እንደማይችል ገልጸዋል።

ወደ ውድድሩ ቦታ የሚመጡ ተሳታፊዎች የሙቀት ልኬት የማድረግ እንዲሁም የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭምብል የእጅ ማጽጃ ኬሚካል (ሳኒታይዘር) እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ተሳታፊዎችን በቲሸርት የቀለም አይነት ከመለየት ባለፈ ለእያንዳንዱ ተሳታፊ በፊደል ተራ የውድድር መለያ ቁጥር ተዘጋጅቷል።

በመለያው አማካኝነት ተሳታፊዎች በአንድ ሺህ በተለያዩ ቡድን በመከፋፈል አካላዊ ርቃታቸውን ጠብቀው ውድድሩን እንዲጀምሩ ይደረጋል ብለዋል።

የተሳታፊዎችን የእርስ በእርስ ንክኪ ለመቀነስ የውድድሩ ተታፊዎች እንደለበሱት የቲሸርት ቀለም ቅደም ተከተል መሰረት በተለያየ ሰዓት እንደሚነሱም ነው አቶ ኤርሚያስ ያስረዱት።

ከዚህ በፊት በነበሩ ውድድሮች ከጤና ሯጮች በአትሌቶች ውድድር 500 ተሳታፊዎች እንደነበሩና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት አትሌቶቹ ወደ 300 ዝቅ እንዲሉ መደረጉን አመልክተዋል።

አትሌቶች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፉም ጠቁመው፤ ውደድሩ ከተጠናቀቀ በኋላም የሽልማት ስነ ስርዓት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ይከናወናል ብለዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሕክምና ቡድን ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በመሆን የጤና እክል ለሚገጥማቸው አትሌቶችና የጤና ሯጮች ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።

የቀይ መስቀል ጣቢያዎቹ ውድድሩ በሚያካልላቸው የተለያዩ መንገዶች ላይ እንደሚኖሩም አስረድተዋል።

የዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስቀል አደባባይን መነሻውን አድርጎ ፍጻሜውን አትላስ ሆቴል አካባቢ ይሆናል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም