ከህግ መውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግር ትክክለኛ መረጃ ተጣርቶ በአስቸኳይ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ምክር ቤቱ አዘዘ

1761

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከህግ መውጫ ፈተና ጋር በተያያዘ የተከሰተውን ችግር ትክክለኛ መረጃ የሚመለከታቸው አካላት በአስቸኳይ አጣርተው ለህዝብ ይፋ እንዲያደርጉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዘዘ።

በምክር ቤቱ የሰው ሃብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከሰሞኑ ከህግ መውጫ ፈተና ጋር በተገናኘ ህይወቱን ያጠፋውን አይነ ስውር የህግ ተማሪ አብርሃም ደሬሳ መነሻ ችግር ላይ የሚመለከታቸውን ጠርቶ ማብራሪያ ጠይቋል።

ችግሩ የፈተናዎች ኤጀንሲ የህግ መውጫ ፈተና ከሰጠባቸው አንዱ በሆነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጊቢ ውስጥ የተከሰተ ነው።

አብርሃም ዱሬሳ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ዲግሪውን እንዳገኘ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት የመውጫ ፈተና በመውሰድ ላይ እንደነበር ተነግሯል።

ቋሚ ኮሚቴው ችግሩ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ፣ ከተፈጠረ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎች፣ ችግሩ የማን እንደሆነና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሃላፊዎችን ማብራሪያ ጠይቋል።

የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ ፈተናውን በ2012 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ለመስጠት ቢታቀድም በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በተወሰኑ አካካቢዎች በነበረው የጸጥታ ችግር ሳይሰጥ መቅረቱን አውስተዋል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ ፈተና ጣቢያ ማገልገሉን ጠቅሰው፤ ለአይነ ስውራን አንባቢ ማዘጋጀትን ጨምሮ ፈተናውን መስጠት የሚያስችሉ አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጉን ጨምረው ገልጸዋል።

ለተማሪ አብርሃምም ኤጀንሲው በተመደበው አንባቢ አማካኝነት ከታህሳስ 13 እስከ 16 ቀን 2013 ዓ.ም የሚሰጠውን ፈተና የመጀመሪያዎቹን 3 ቀናት በሰላም መውሰዱን አብራርተዋል።

ይሁን እንጂ በፈተናው የመጨረሻ ቀን ፈተናው የሚጀመረው 3 ሰአት ቢሆንም አንባቢው ፈተናው ከተጀመረበት እስከ 45 ደቂቃ ድረስ ሊያገኘው እንዳልቻለ አስረድተዋል።

ከ45 ደቂቃ በኋላ አንባቢውን ማግኘቱንና በፈተና መመሪያ መሰረት አንድ ተማሪ ማርፈድ የሚችለው 30 ደቂቃ በመሆኑ ፈተናውን መቀመጥ አለመቻሉን ገልጸዋል።

ተማሪው በወቅቱ የፈተና ጣቢያ ሃላፊንና ፈታኙን አግኝቶ ከጊቢው እንደወጣና ህይወቱን ማጥፋቱን በመገናኛ ብዙሃን እንደማንኛውም ሰው መስማታቸውን ዋና ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው አንስተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ ይህን ይበሉ እንጂ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ወሰን አለሙ ተማሪ አብርሃም ዩኒቨርሲቲ ጊቢ የደረሰው 3 ሰዓት መሆኑን ማህበሩ መረጃ እንዳለው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የፈተና ኮድ ባለመያዙ ምክንያት ወደ ቤቱ መመለሱንና የፈተና ኮድ ይሁን ወይንም መታወቂያ ግን መረጃ እንዳሌላቸው አስረድተው በ40 ደቂቃ ውስጥ መመለሱን ጨምረዋል።

በዚህ ጊዜ የተማሪው አይነ ስውርነት ከግምት ውስጥ ገብቶ ፈተናውን እንዲወስድ ማድረግ ይቻል እንደነበር ጠቅሰው፤ መመሪያ ካልፈቀደም ክፍተቱ የመመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በፍትህ ማሻሻያ መርሃ ግብር ውስጥ ከታዩ ጉዳዮች አንዱ የህግ መውጫ ፈተና መሆኑን በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል።

ተማሪ አብርሃም ዱሬሳ ፈተናውን የወሰደው ለሶስተኛ ጊዜ እንደሆነና ፈተናው በዚህ አመት የተሰጠው በ2012 ዓ.ም መፈተን ለነበረባቸው መደበኛና ከዚህ በፊት ባሉት አመታት ፈተናውን ማለፍ ላልቻሉ እንደ ተጨማሪ እድል ተሰጥቶ መሆኑን አብራርተዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ ዩኒቨርሲቲው ያለአግባብ ስሙ ተነስቷል ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል።

ፈተና በሚሰጥበት የዩኒቨርሲቲ ጥበቃዎች ተማሪውን እንዳይገባ አለመከልከላቸውን እንዳጣሩ ጠቅሰው፤ ይሁን እንጂ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዩኒቨርሲቲው ጥፋተኛ እንደሆነ ተደርጎ መቅረቡ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ማብራሪያ መሰረት በማድረግ ትክክለኛውን መረጃ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ኮሚቴ በማቋቋም በአስቸኳይ አጣርተው እንዲያቀርቡ ቋሚ ኮሚቴው አዟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተወካይ አቶ ማዘንጊያ እያቶ “ለችግሩ አንዱን ከሳሽ አንዱ ተከሳሽ ማድረግን ትቶ” በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መሪነት ጉዳዩን በማጣራት ለህዝብ ይፋ እንዲሆን አሳስበዋል።

በዚህም ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ ከአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሚሰሩ ማህበራት ኮሚቴ በማቋቋም በትክክል የተፈጠረውን ሪፖርት እንደሚያቀርቡ አስገንዝበዋል።

በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ችግር የፈጠሩ አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ከዚህ በመነሳት ለቀጣይ ትምህርት እንዲሆን አሰራሮችና አዋጆች መፈተሽ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።