የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተጎጂዎችን ሊጎበኙ ነው

1626

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የጸጥታ ችግር ተከስቶባቸው ወደነበሩ የአገሪቷ አካባቢዎች በማቅናት ከተጎጂዎችና ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር ሊወያዩ ነው።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ዛሬ በጉዳዩ ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጉባኤው ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በአገሪቷ ባለፉት ጊዜያት በተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች የዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ በርካቶች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውንና ንብረታቸውም መውደሙን አንስተዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የአገር ሽማግሌዎች መማክርት እነዚህን ተጎጂዎች ለመጎብኘትና ለመወያየት ውሳኔ ላይ መደረሱን ተናግረዋል።

በነገው ዕለትም ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን በማቅናት ውይይቱ በይፋ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

ቁጥራቸው 25 የሚሆኑ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ያካተተው የልዑካን ቡድን ወደ ሥፍራው አቅንቶ ተጎጂዎችን እንደሚያነጋግርም አስታውቀዋል።

“በመቀጠልም ቡድኑ ወደ ትግራይ ክልል፣ ወደ ማይካድራ እንዲሁም ደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሌና አፋር ክልሎች ያመራል” ብለዋል።

ጉብኝቱ በዋናነት ተጎጂዎችን ማግኘት፣ ማወያየትና ማጽናናት ዓላማ ያደረገ ሲሆን ተጎጂዎቹ የደረሰባቸውን ጉዳት በመለየት ድጋፍ ለማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር እንደሚደረግ ነው ዋና ጸሐፊው የገለጹት።

ጎን ለጎንም አገር በቀል እውቀቶችና ክህሎቶች የጸጥታ ችግሮችን አስቀድሞ ለመከላከል እንዲሁም ግጭት ከተከሰተ በኋላ እንዳይዛመት ለማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ይሰራል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ሻለቃ አትሌት ኃይሌገብረሥላሴ በበኩሉ “የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮች መደገም የለባቸውም” ብሏል።

ለዚህም ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበት ጠቁሞ፤ የጥላቻ መልዕክት የሚያስተላልፉ ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸው አስገንዝቧል።

በተለይም በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ መልዕክቶች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው እንደሚገባና በኃላፊነት ስሜት መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

“የጉብኝት መርሃ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን ማኅበረሰቡ፣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችን ሊሰማ ይገባል” ብሏል።

ኅብረተሰቡ የቆየ የአብሮነትና የአንድነት እሴቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ በጋራ ጥምረቱ በኩል በትኩረት እንደሚሰራም በመግለጫው ተመልክቷል።