የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር አዲስ ከንቲባ ሾመ

231
ባህርዳር ሀምሌ 15/2010 የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አዲስ ከንቲባና ምክትላቸውን ሾመ፡፡  ምክር ቤቱ ሹመቱን የሰጠው 14ኛ መደበኛ ጉባኤውን ሲጠናቅቅ ነው። በዚህም የአገልግሎት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁትን የቀድሞው የከተማዋ ከንቲባ አቶ አየነው በላይን በማሰናበት አቶ ሙሉቀን አየውን የከተማዋ ከንቲባ ፣አቶ አለም ታደሰን ደግሞ ምክትል አድርጎ ሾሟል፡፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ  አቶ ፍታ ነገስት በዛብህ እንደገለጹት አዲሱ ተሿሚ ከንቲባ ከ30 ዓመታት በላይ በአመራርነትና በባለሙያነት ያገለገሉና የተሻለ የአመራር ልምድ ያካበቱ  ናቸው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በእንግሊዘኛ ቋንቋና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በትምህርት እቅድ ስራ አመራር የሰሩት አቶ ሙሉቀን በምዕራብ ጎጃም ዞን መምህራን ማህበር ሊቀመንበርና የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል። በመንግስትም የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ፣ የትምህርት መምሪያ ኃላፊና የአማራ ክልል ሲቪል ሰርቪስ የሰው ኃይል ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ሆነው ማገልገላቸውም ተመልክቷል። በአዲስ የተሾሙት  ከንቲባ ባደረጉት ንግግር በከተማዋ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግርና የወጣቶችን ስራ አጥነት ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ለመስራት ቃል ገብተዋል። የኑሮ ውድነት፣የመሰረተ ልማት ለማፋጠንና  ከተማዋን የበለጠ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት ከሚሰሯቸው መካከል የጠቀሱት አቶ አየነው ለዚህ የህብረተሰቡ እገዛ በተለይም ወጣቱ ከጎናቸው እንዲሆን መልዕክታቸውን  አስተላልፈዋል። ምክር ቤቱ በተጨማሪም  አቶ ባየ አለባቸውን የከተማዋ ቴክኒክና ሙያ  ኢንተር ፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አድርጎ ሹሟል። ከሐምሌ 12 /2010ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የምክር ቤቱ መደበኛ  ጉባኤ የከተማዋን የአካባቢና ማህበራዊ ደህንነት አፈጻጸም መመሪያ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ መረሀ ግብሩን አጠናቋል  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም