መገናኛ ብዙሃን የአገር ሰላምንና አብሮነትን በማጎልበት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ አይደለም ተባለ

81

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን የአገር ሰላምና የህዝቦችን አብሮነትን በማጎልበት ረገድ የሚጠበቅባቸውን ሚና እየተወጡ አይደለም ተባለ።

ይህ የተገለጸው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዛሬ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በውይይቱ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የመገናኛ ብዙሃን በአገራዊ ሰላምና በህዝቦች አንድነት ላይ ያላቸው ሚናን በሚመለከትም ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መገናኛ ብዙሃን እውነተኛ መረጃ ከማሰራጨት ይልቅ የህዝቦችን አብሮነት የሚሸረሽሩ ዘገባዎችን እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

መገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጯቸው መረጃዎች በዜጎች ደህንነት ላይ የሚፈጥሩትን አደጋ ሊገነዘቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

'እኛና እነሱ' በሚል አስተሳሰብ የሚሰራጩ የተሳሳቱ ዘገባዎች በርካታ ንጹሃን ላይ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት እንደሆኑም አስገንዝበዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ሙላቱ አለማየሁ በበኩላቸው የፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች በሚዲያ ቀርበው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የጥላቻ ንግግሮችን ሲያስተላልፉ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

"አብዛኞቹ የጥላቻ ንግግሮችም በዜና መልክ ለህዝቡ የሚቀርቡ ናቸው" ብለዋል።

በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ለሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ ግጭቶች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቅርቡ 15 ያህል መገናኛ ብዙሃን ላይ በተደረገ ጥናት 28 በመቶ የሚሆኑት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

18 በመቶው የሚሆነው ሽፋናቸው ደግሞ በግጭቶችና ከዚያ ጋር ተያይዞ በሚከሰቱ ሰብዓዊ ቀውሶች ላይ ትኩረት ያደረጉ መሆናቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

"ጥናቱ መገናኛ ብዙሃን ለሰላም መስፈን ያበረከቱት አስተዋጽኦ ዝቅተኛ መሆኑንም አመላክቷል" ብለዋል።

"የመገናኛ ብዙሃን አሰራር በሚፈለገው ልክ አለመዘመን ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ አድርጓል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ወንድወሰን አንዷለም ናቸው።

የሚዲያ ስነ-ምግባር ከየትኛውም ሃይማኖት አስተምዕሮ ጋር የሚጣጣም በመሆኑ በተለይ የህብረተሰቡን መልካም እሴቶች አጉልቶ በማውጣት ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃኑ ህግና ስርዓትን አክብረው ለሰላምና መረጋጋት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶችም መገናኛ ብዙሃን ለአገሪቷ ሰላምና ለህዝቦች አንድነት የተጣለባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጰያ አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃን ግጭቶችን አስቀድሞ መከላከል የሚችሉ ዘገባዎችን በመስራት ረገድ ውስንነት ያለባቸው ሲሆን፤ 90 በመቶ የሚሆኑ ከግጭት ጋር የተያያዙ መረጃዎች የሚያሰራጩት ግጭቱ ከተከሰተ በኋላ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም