በዲላ ከተማ ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ግንባታ ሊካሄድ ነው

1710

ዲላ፣ ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ ከ266 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመጠጥ ውሀ ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሄድ ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የፕሮጀክቱን ግንባታ  በሁለት ዓመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተቋራጩ ጋር የውል ሥምምነት የፊርማ ሥነ-ሥርዓትም ተካሄዷል።

የከተማዋን የንጹህ መጠጥ ውሃ ለመፍታት ለሚገነባው ፕሮጀክት የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡት የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅቱ  እንዳሉት የውሃ ፕሮጀክቱ የዲላ ከተማን የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያግዝ ነው።

ግንባታው ሲጠናቀቅ  የመጠጥ ውሃ   እጥረቱን ከመፍታት ባለፈ ዲላ  ከተማን ለኢንቨስትመንት ተመራጭ እንደሚያደርጋት ገልጸዋል።

መንግስት ከህዝቡ የሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሰራ እንደሚገኝ የተናገሩት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ  ፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ የከተማዋ ነዋሪዎችና በየደረጃው የሚገኝ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በመሰረተ ልማት ተቋማት ግንባታ ወቅት ማነቆ የሆነው የወሰን ማስከበር ጥያቄ በውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ሁሉም ተባባሪ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት ግንባታው በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የክልሉ ውሀና ማዕድን ቢሮ ሀላፊ አቶ አክሊሉ አዱኛ በበኩላቸው ግንባታውን በሁለት ዓመት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተቋራጩ ጋር ውል መገባቱን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ የጥልቅ ውሀ ጉድጓድ ቁፋሮን ጨምሮ 65 ኪሎ ሜትር ከፍተኛና የከተማ ውስጥ የባንቧ መስመር ዝርጋታ፣ ከሶስት ሺህ እስከ ሶስት ሺህ አምስት መቶ ሜትር ኩብ ውሀ የሚይዙ ሁለት ማጠራቀሚያ ገንዳዎች የውሀ መሳቢያ ሞተሮች ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።

ግንባታው በ”ማቺንግ ፈንድ” መዋጮ እና ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር ጨምሮ  266 ሚሊዮን 374 ሺህ ብር ወጪ  የሚከናወን መሆኑን አቶ አክሊሉ አስረድተዋል።

የጌዴአ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ  ፕሮጀክቱ የዘመናት የዲላ ከተማ ነዋሪ ጥያቄ የሆነውን የውሀ አቅርቦት ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

ግንባታውን የሚያከናውነው ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል ወርቁ ግንባታውን ከተቀመጠለት ጊዜ ገደብ አስቀድመው በማጠናቀቅ  ለማስረከብ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት የክልሉና የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።