የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኞች ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋገጡ

1577

አዲሳ አበባ ሐምሌ 15/2010 የችግኝ ተከላ ለአረንጓዴ ልማት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ከመትከል ባሻገር እንዲጸድቁ በመንከባከብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ሰራተኞች ገለጹ።

የድርጅቱ ሰራተኞች ዛሬ በፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ድሬ ግድብ ላይ ከ2ሺህ በላይ ችግኞችን ተክለዋል።

ድርጅቱ ዘንድሮ የችግኝ ተከላ ሲያካሄድ ለ15ኛ ጊዜ ሲሆን “አንድ ችግኝ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” በሚል መሪ ሃሳብ የችግኝ ተከላውን አከናውነዋል።

ሰራተኞቹ እንዳሉት የችግኝ ተከላ ሥራ የተራቆተ መሬትን በደን ከማልበስ በተጨማሪ በከተሞች አካባቢን የሚያስውብ ነው።

”አረንጓዴ አካባቢዎችንና ደኖችን ማስፋፋትና መንከባከብ የሁሉም ድርሻ ሊሆን ይገባል” ያሉት ሰራተኞቹ ፤ በዚህም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነው የገለጹት።

የድርጅቱ ሰራተኛ አቶ ገብረእግዚአብሄር ገብረስላሴ እንደገለጹት፤ በተለያዩ ጊዜ ተቋማት ችግኝ በመትከል ተግባር ይሳተፋሉ፤ ይሁንና ከመትከል ባሻገር እንክብካቤ የማድረግ ስራው ትኩረት አይሰጠውም።

ሌላዋ የድርጅቱ ሰራተኛ ወይዘሮ በየነች በላይ በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ የመከታተልና የመንከባከብ ተግባር እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

አቶ ይልማ ወልደገብርኤል በበኩላቸው በአገሪቱ አረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በየአካባቢው ችግኞችን የመትከልና የመንከባከብ ተግባር እንዲያከናውኑ ጠይቀዋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተካ አባዲ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የችግኝ ተከላ ስራ ቀደም ባሉት ዘመናት በተለያዩ ስፍራዎች ላይ ሲከናወን ቆይቷል።

የአረንጓዴ ልማት መስፋፋት በተለይም ለህትመት አገልግሎት የሚውሉ ወረቀቶችን ለማምረትና ለመጠቀም የሚያስችሉ ግብአቶችን ለማግኘት የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትም የችግኝ ተከላ ዘንድሮ ለ15ኛ ጊዜ ሲያከናውን በዚህ ጊዜ ውስጥ ችግኞቹን ከመትከል ባሻገር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀትና በየ3 ወሩ ቦታው ላይ በመገኘት ችግኞቹን የመከታተል ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በመሆኑን ደኖችን በመትከልና መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል አገርንም አካባቢንም በመጥቀም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።