አገር አቀፍ የወጣቶች የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በመላ አገሪቷ የሚገኙ ወጣቶች የሚሳተፉበትን የንግድ ስራ ፈጠራ ውድድር ይፋ አደረገ።

ለውድድሩ 20 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል።

በመጪዎቹ ሶስት ዓመታት የሚካሄደው ውድድር ወጣቶች ለስራ እንዲነሳሱ ንቅናቄ የመፍጠር አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገልጿል።

የኮሚሽኑ የአዳዲስ ስራ ዕድሎች ፕሮጀክት ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምጸሀይ ደርሶልኝ እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ 200 ከፍተኛ የማደግ ብቃት ያላቸው የንግድ ፈጠራ ሀሳቦችን የሚያመነጭ ውድድር ያካሂዳል።

"የብሩህ ስራ ፈጠራ ሀሳቦች ውድድር" በሚል በተዘጋጀው በዚህ ውድድር አንድ ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ" ብለዋል።

የውድድሩ ምዝገባ በሚቀጥለው ወር እንደሚካሄድም ጠቁመዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረገው ውድድር 20 የስራ ፈጠራ ሀሳቦች እንደሚቀርቡ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

"ውድድሩን የሚያልፉ ወጣቶች ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖ የአንድ ወር ስልጠና እንደሚሰጣቸው ጠቅሰው፤ ከተሳታፊዎቹ የተሻለ ውጤት የሚያገኙት ደግሞ ሽልማት ያገኛሉ" ብለዋል።

የኮሚሽኑ ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ሙሉጌታ ፕሮጀክቱ በተለይ የሴቶች፣ የአካል ጉዳተኞችና የተፈናቃይ ወጣቶችን ተሳትፎ እንደሚያበረታታ አስታውቀዋል።

ለሽልማት ከሚውለው ገንዘብ 300 ሺህ ዶላር ያህሉ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የተገኘ ሲሆን፤ መንግስት አንድ ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡን ገልፀዋል።

ከተለያዩ ድርጅቶችም 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም