ኅብረተሰቡ በበዓል ግብይትና በዕርድ ወቅት ራሱን ከኮሮናቫይረስ መጠበቅ ይገባዋል

97

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኅብረተሰቡ ለገና በዓል ግብይትና ዕርድ ሲፈጽም ጥንቃቄ በማድረግ ራሱን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል እንዳለበት የግብርና ሚኒስቴር አሳሰበ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በበዓል ግብይት መጨናነቅና የገንዘብ ልውውጥ ስለሚበዛ ኅብረተሰቡ ተገቢውን የኮሮናቫይረስ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።

"በግብይት ወቅትም ሆነ የእንስሳት እርድ ሲፈጸም ንክኪ ስለሚበዛ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ እንዲሁም ሳኒታይዘር መጠቀም ግድ ይላል" ብለዋል።

"ኅብረተሰቡ የእርድ እንስሳትን ሲገዛ በተቻለው መጠን ጤናማ መሆናቸውን በመለየት ጥንቃቄ ማድረግ አለበት" ያሉት ዶክተር ፍቅሩ፤ የእንስሳት እርድ በቄራዎች መከናወን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የበግና የፍየል እርድ በቤት ውስጥ ሲካሄድ ኮሮናቫይረስ መከላከልን መሰረት ባደረገ መልኩ መሆን እንዳለበትም አመልክተዋል።

ዶክተር ፍቅሩ ኅብረተሰቡ ከሌሎች ተላላፊ በሽታዎችም ራሱን ለመከላከል ጥሬ ሥጋ ከመመገብ እንዲቆጠብ መክረዋል።

ሥጋን አብስሎ መመገብ በንክኪ ከሚመጣ የኮሮናቫይረስ መከላከል ከማስቻሉ ባለፈ ከእንስሳት ወደ ሰው ከሚተላለፉ ሌሎች በሽታዎች ለመጠበቅ እንደሚያግዝም አስረድተዋል።

በእርድ ወቅት ቆዳና ሌጦ እንዳይበላሽ እንዲሁም እርድን ተከትሎ የአካባቢ ብክለት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም