የሚኒስቴሩ አመራር አባላት በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጎበኙ

64

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አመራር አባላት በሰሜን ዕዝ ላይ በተፈፀመው ጥቃት ጉዳት የደረሰባቸውን የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአዲስ አበባ የጦር ሃይሎች ሆስፒታል ተገኝተው ጎበኙ።

ሚኒስቴሩ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታሉ ለሚገኙ የሠራዊቱ አባላት የገና በዓል ስጦታ አበርክቶላቸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ ወይዘሮ ሕይወት ሃይሉ በጉብኝታቸው ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ማየት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጉብኝት ባለፈ የስነ-ልቦና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንና ሴት ጀግኖችንም በተለያየ መንገድ እንደሚያበረታታ ተናግረዋል።

የጦር ሃይሎች ሆስፒታል ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል እየሰጠ ያለው አገልግሎትና ለሠራዊቱ አባላት እያደረገላቸው ያለው የሕክምና ክትትል መልካም እንደሆነም ገልፀዋል።

ሚኒስቴሩ ሴት የሠራዊቱን አባላት በቋሚነት ለመደገፍ ከተለያዩ አካላት ጋር እየመከረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ድጋፉ ለሠራዊቱ አባላት የሞራል ስንቅ የሚሆንና ለበለጠ ግዳጅ የሚያነሳሳ እንደሚሆን ተናግረዋል።

'ከጎናችሁ ነን' በማለት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ሠራዊቱን ለበለጠ መስዋዕትነት የሚያነሳሳ መሆኑን ነው የገለጹት።

በሆስፒታሉ ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት እየተሰጠ ያለው የሕክምና አገልግሎት ጥሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ከጉብኝቱ በኋላ የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ስጦታ ለሠራዊቱ አባላት አበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም