የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለመከላከያ ሠራዊት 3 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከተ

67

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27/2013 ( ኢዜአ)  የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ለአገር መከላከያ ሠራዊት የ3 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አበረከተ።

2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተበረከተ ሲሆን ከዚሁ ውስጥ 500 ሺህ ብር ለሴት የመከላከያ ሠራዊት አባላት የተደረገ ነው።

በተጨማሪም ለሴት የሠራዊቱ አባላት 500 ሺህ ብር የሚገመት የንጽህና መጠበቂያና የተለያየ ቁሳቁስ ለሰራዊቱ ተበርክቷል።

የሴቶች፣ ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ፊልሰን አብዱላሂ "የሠራዊቱ አባላት ለአገር የከፈሉትና እየከፈሉ ያለው ዋጋ ትልቅ በመሆኑ ሁሌም ልናመሰግናቸውና ልናግዛቸው ይገባል" ብለዋል።

"በተለይም ሴት የሠራዊት አባላት ከወንዶቹ ባልተናነሰ መልኩ እየፈፀሙት ያለው ጀግንነት ለሁላችንም ኩራት ነው፤ የዛሬው ድጋፍም አብሮነታችንን ለማሳየት ያደረግነው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታዋ ማርታ ሉዊጂ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

"የመከላከያ ሠራዊቱ የተሰጠውን ተልዕኮ በስኬት እንዲወጣ በየአቅጣጫው እየተደረገለት ያለው ድጋፍ ላቅ ያለ ሚና አበርክቷል" ያሉት ወይዘሮ ማርታ፤ የሕዝቡ ድጋፍ በቀጣይም ለሠራዊቱ ሞራል ሆኖ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

በመከላከያ ሚኒስቴር የሴቶች ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ በበኩላቸው በሕግ ማስከበር ተግባሩ ሴት የሠራዊቱ አባላት ያሳዩት ተጋድሎ ሠራዊቱ ለሕዝቡ ሠላም የትኛውንም ዋጋ እንደሚከፍል የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም