የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈጥሯቸው የስራ እድሎች ላይ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራን ነው-የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ

101

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27/2013 ( ኢዜአ) በመዲናዋ የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች በሚፈጥሯቸው የስራ እድሎች ላይ ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ቢሮ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በሴቶች ተጠቃሚነት ዙሪያ ውይይት አካሄዷል።።

የውይይቱ ዋነኛ ዓላማ  በፖለቲካ ዘርፍና በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማሳደግ መሆኑ ተገልጿል።

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሀዳስ ኪዱ በዚህን ወቅት ሴቶችን በኢኮኖሚውና በፖለቲካው ዘርፍ ከወንዶች እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይ ከለውጡ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በምክር ቤት የሴቶች ተሳትፎ 37 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል።

በክፍለ ከተማ ደረጃ የሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ  ከዚህ በፊት ከነበረበት 18 በመቶ ወደ 37 በመቶ ከፍ ማለቱን ነው የተናገሩት።

በወረዳ ደረጃም ተሳትፏቸው 48 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል።

በመዲናዋ እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ላይም ሴቶች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ እድል እንዲያገኙም ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ሸገር ዳቦ ፋብሪካ፣ የእንጦጦ ፓርክ ፕሮጀክት እንዲሁም ጀሞ ሁለገብና ፉሪ ሁለገብ የገበያ ማዕከላትን ለአብነት አንስተዋል።

በመዲናዋ ለ27 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ ፕሮጀክቶች በቅርቡ እንደሚገነቡ ገልጸው፤ የስራ እድል ከሚፈጠርላቸው መካከል ግማሽ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪ ቢሮው በመዲናዋ በሚገኙ አስራ አንድ ክፍለ ከተሞች ላይ "ደስተኛ ህጻናት ለአዲስ አበባ" የሚል መሪ ሀሳብ የህጻናት ስብዕና መገንቢያ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በውይይት መድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህጻናት ቢሮ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ተገምግሞ የቀጣይ ስድስት ወራት የስራ አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም