በሀዋሳ የገና በዓል ግብይት የተረጋጋ መሆኑን ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ

579

ሀዋሳ፣ ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ የገና በዓል ግብይት በዋጋ ሆነ በምርት አቅርቦት ተመጣጣኝና በቂ ሆኖ የተረጋጋ ሂደት ላይ እንደሚገኝ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ። 

በሀዋሳ ከተማ ገበያ ሲገበያዩ ከነበሩት መካከል መምህር ተቀባ ማርቆስ እንዳሉት በከተማዋ ባሉ የገበያ ስፍራዎች  እንደ ወትሮው የበዓል ግብይት ወከባ ያልበዛበትና የተረጋጋ ነው።

በገና በዓል ግብይት ከዚህ በፊት በበዓላት ወቅት ይታይ የነበረው የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ፣ ይልቁንም እንደ ሽንኩርት ያሉ ምርቶችን ከሳምንታት በፊት በነበረው ዋጋ መሸመታቸውን ገልፀዋል።

በከተማዋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ክፍት በተደረገው  የንግድ ትርኢትና ባዛር ሲገበያዩ የነበሩት ወይዘሮ ሙና ስዩም በበኩላቸው ባዛሩ ለሸማቾች ተጨማሪ የግብይት ቦታ በመሆን አማራጫቸውን እንዳሰፋላቸው ተናግረዋል።

በባዛሩ ውስጥ በቂ ምርቶች መቅረባቸውንና በቅናሽ ዋጋ እየተገበያዩ መሆኑን አክለዋል።

ሆኖም የበዓል ግብይት እንቅስቃሴዎች ላይ በርካታ ሰዎች ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ተግባራዊ ሳያደርጉ እንደሚገበያዩ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

በባዛሩ አልባሳትና ሌሎች ለበዓል የሚሸመቱ እቃዎችን ይዘው የቀረቡት አቶ ቶማስ አቅሴቦ በሰጡት አስተያየት  የተለያዩ አልባሳትን በቀጥታ ከፋብሪካዎች በማስመጣት በተመጣጣኝ  ዋጋ ለሸማቹ  ማቅረባቸውን ገልፀው ሸማቾችም ደስ ብሏቸው እየሸመቱ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የበዓል ግብይቱ ይቀዛቀዛል የሚል ሥጋት አድሮባቸው የነበረ ቢሆንም ጥሩ የንግድ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁመዋል።

በሀዋሳ አትክልት ገበያ በጅምላ አከፋፋይነት ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አበበ ወቼ እንደተናገሩት ምርቶቹን በተመጣጣኝ ዋጋ በማስመጣት በተመጣጣኝ ዋጋ ለቸርቻሪዎች እያከፋፈሉ ነው።

ከዚህ በፊት በበዓል ወቅት እንደሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ዘንድሮ አለመከሰቱን ጠቅሰው አትክልቶችን ከሚያስመጡበት ስፍራ በቂ ምርት መኖሩን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወጤ ቶሼ ወቅቱ የመስኖና የመኸር ምርቶች በብዛት ወደ ገበያ የሚቀርብበት መሆኑ  ለሸማቾችና ነጋዴዎች ምቹ  ሁኔታን መፍጠሩን ገልጸዋል።

የፋብሪካ ውጤቶችም ቢሆኑ በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው እየቀረቡ እንደሆነ ጠቁመው በገና በዓል ግብይት ከወትሮው በተሻለ መረጋጋት የሚታይበት  ነው ብለዋል።

አሁን ላይ መጠነኛ ጭማሪ ከታየበት ጤፍ በስተቀር በተለይ የአትክልት ምርቶች ከአምናው የበዓል ወቅት ዝቅ ባለ ዋጋ እየተሸጡ  መሆኑን ተናግረዋል።

ቅቤና ሌሎች ለበዓል የሚያስፈልጉ  ምርቶችም ቢሆን መጠነኛ ጭማሪ ቢታይባቸውም ከወቅታዊ ሁኔታው ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ እንደሆነ አስረድተዋል።

ያልተገባ ዋጋ የሚጨምሩና ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ደባልቀው ለገበያ የሚያቀርቡ ግለሰቦችን ለመቆጣጠርም ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በሀዋሳ ከተማ የተዘጋጀው የንግድ ትርኢትና ባዛርም ለሸማቾች የአቅርቦትና የዋጋ አማራጭ ከመፍጠሩም ባለፈ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የተቀዛቀዘውን የገበያ ሁኔታ እያነቃቃው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ እንዳመለከቱት በዝግጅቱ ከ140 በላይ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ጨምሮ የተለያዩ ፋብሪካዎች ምርቶች  ይዘው የቀረቡ ነጋዴዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።