ኮሚሽኑ ለመተከል ተፈናቃዮች ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

1737

አሶሳ፣ ታህሳስ 27/ 2013( ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የመተከል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት በዘላቂነት እንደሚደግፍ አስታወቀ፡፡

በኮሚሽኑ የአሶሳ ንዑስ ቢሮ ሃላፊ ሚስ ጆላንዳ ቫን ለኢዜአ እንደተናገሩት  ኮሚሽኑ የመተከል ተፈናቃዮችን ለመደገፍ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡

በክልሉ  የተለያዩ የተባበሩት መንግስታት ረጂ ድርጅቶች እንዳሉ የጠቀሱት ሃላፊዋ ድጋፉን ለማጠናከር ቅንጅታዊ አሰራር ፈጥረን እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል፡፡

ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ ለዞኑ ተፈናቃዮች ምግብ ነክ ያልሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አውስተዋል፡፡

የመተከል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም መንግስት የሚያደርገውን ጥረት ኮሚሽኑ በቀጣይም በዘላቂነት እንደሚደግፍ ሚስ ጆላንዳ አስታውቀዋል፡፡

ከኮሚሽኑ ጋር በመቀናጀት ለመተከል ተፈናቃዮች ድጋፍ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት መካከል አክሽን ፎረ ዘ ኒዲ የተባለ ረጂ ድርጅት የአሶሳ ቅርንጫፍ አንዱ ነው፡፡

የቅርንጫፉ ሃላፊ አቶ መላኩ ገዛኸኝ እንዳሉት ድርጅቱ ሰሞኑን ለመተከል ተፈናቃዮች ባደረገው የመጀመሪያ ዙር እገዛ  የተለያዩ ቁሳቁሶችን በድጋፍ አቅርቧል፡፡

ከቁሳቁሶች መካከል የምግብ ማብሰያ እና መመገቢያ ቁሳቁሶች፣ አልባሳት፣ ፍራሽ፣ የአልጋ አጎበር እና ሌሎችም ለክልሉ አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽን ማስረከቡን ጠቅሰው ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት እና ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ተሲሳ በበኩላቸው በክልሉ የመተከል ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋም መንግስት ብቻውን የሚወጣው ባለመሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የማሳተፍ ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ድርጅቶቹ ለቀረባላቸው ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ እየሰጡ ነው ብለዋል፡፡

ድጋፉን እያደረጉ ከሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እና አብረው የሚሰሩት ድርጅቶች ዋነኞቹ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ድጋፉን በክላስተር በመለየት ለማሰባሰብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው ድጋፉን ወደ መተከል በቀጥታ ማድረስ የማይችሉ ድርጅቶች በአሶሳ እና አካባቢው እንዲያስረክቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

እስካሁን በርካታ ምግብ እና ቁሳቁሶች በድጋፍ መሰብሰባቸውን ጠቁመዋል፡፡

በቅርቡ የተሰባሰበው ድጋፍ ወደ መተከል ቡለን እና ድባጤ ለማድረስ እየተሠራ መሆኑን አቶ ታረቀኝ  አስረድተዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቀደም ሲልም ለመተከል ተፈናቃዮች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን በወቅቱ ተገልጿል።