ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ጎንደር ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ አቅርበዋል

63

አዲስ አበባ ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውን የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ፡፡

የከተማዋ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ አቶ ባዩ አቡሃይ ለኢዜአ እንዳሉት በአገሪቷ ከፍተኛ የቱሪስት ፍስት ከሚታይባቸው ከተሞች ጎንደር ቀዳሚ ብትሆንም በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠቃሚ አልነበረችም፡፡

በተለይም በአካባቢው ከዓመታት በፊት የነበረው አለመረጋጋት በኢንቨስትመንት ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለመፍታት ከኅብረተሰቡ ጋር በሰራው ቅንጅታዊ ስራ የአካባቢው ሠላም በመረጋገጡ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ባለሀብቶችን ለመሳብና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማሳደግ ሠላሙን ከማረጋገጥ ጎንለጎን የአካባቢውን እምቅ ሀብት በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ ስራ መስራቱን ገልፀዋል፡፡

በአካባቢው ለኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ የሚሆን በርካታ ግብዓት መገኘቱና በቂ የተማሪ የሰው ኃይል አቅርቦት መኖሩ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፉት ሁለት ዓመታት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ባለሀብቶች በአካባቢው በተለያዩ የልማት መስኮች ለመሰማራት ያሳዩት ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን አክለዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 33 ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንና 60 ኢንዱስትሪዎች ደግሞ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ ማሽነሪ በማስገባት ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ አምስት ወራት ከ3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 75 ባለሀብቶች በተለያዩ የስራ ዘርፎች ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ጎንደርን የኢንዱስትሪ መዳረሻ ለማድረግ የበለጠ እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ባዩ በተለይም በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግና ሌሎች ዘርፎች መሰማራት ለሚሹ አካላት ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

ለዚህ ስኬታማነት ከተማ አስተዳደሩ  ከፌዴራልና ከክልል መንግስት ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

በተለያዩ የስራ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሀብቶች በበኩላቸው በአካባቢው ሠላም መሆን በኢንቨስትመንት ስራቸው ተጠቃሚ ከመሆናቸው ባሻገር ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ከፈለኝ በየነ የቢ.ኬ.ቲ.ኤም ኮንክሪት ማምረቻ ስራ አስኪያጅ እና ማንአየሽ ተሰማ የአባይ ጋርመንት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ፡-

ጎንደር በተለይ ለጋርመንትና ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ምቹ መሆኗን ጠቅሰው ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም