ፖል ቴርጋት በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድር በክብር እንግድነት ይገኛል

63

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27/2013 ( ኢዜአ) ኬንያዊው የቀድሞ የረጅም ርቀት ሯጭ ፖል ቴርጋት በ20ኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በክብር እንግድነት እንደሚገኝ ተገለጸ።

20ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጥር 2 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ስራ አስኪያጅ አቶ ኤርሚያስ አየለ 20ኛ ዓመቱን በያዘው የታላቁ ሩጫ ውድድር ታዋቂው የኬንያ አትሌት ፖል ታርጌት በክብር እንግድነት እንደሚገኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።

እ.አ.አ 2000 በሲድኒ በተካሄደው 27ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በ10 ሺህ ሜትር የወንዶች ውድድር ፖል ቴርጋት ከአትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ጋር ያደረጉት የመጨረሻ ሠዓት ትንቅንቅ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ሁሌም የሚታወስ ነው ብለዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዘንድሮ 20ኛ ዓመቱን ሲያከብር ፖል ቴርጋትን በክብር እንግድነት እንደጋበዘውና እሱም ግብዣውን ተቀብሎ በውድድሩ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጫ መስጠቱን ተናግረዋል።

ከፖል ቴርጋት በተጨማሪ ጥሪ የተደረገላቸው አንጋፋ የኢትዮጵያ አትሌቶችና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በአትሌቶች ውድድር ከኢትዮጵያዊያን በተጨማሪ የኬንያና የኤርትራ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው አቶ ኤርሚያስ የጠቆሙት። 

የ51 ዓመቱ ፖል ቴርጋት በመም፣ በአገር አቋራጭና በጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች ስኬታማ የውድድር ጊዜ የነበረው ሲሆን እ.አ.አ 2000 በሲድኒ ኦሊምፒክ ውድድር የ10 ሺህ ሜትር ሩጫ በሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በአንድ ማይክሮ ሴኮንድ ተቀድሞ የተሸነፈበት ውድድር ለአትሌቱም ሆነ ለአትሌቲክሱ ማኅበረሰብ የማይረሳ ታሪክ ነው።

ፖል ቴርጋት በውድድሩ በሻለቃ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ አስደናቂ የአጨራረስ ብቃት የተሸነፈ ሲሆን ሃይሌ 27 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ19 ማይክሮ ሴኮንድ ሲያሸንፍ ኬንያዊው አትሌት 27 ደቂቃ ከ18 ሴኮንድ ከ20 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ መውጣቱ ይታወሳል።

ፖል ቴርጋት እ.አ.አ በ2003 በተካሄደው የበርሊን ማራቶን 2 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ በመግባት በማራቶን የዓለም ክብረወሰን የሰበረ የመጀመሪያው ኬንያዊ አትሌት ነው።


በዘንድሮው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች አንደኛ ለሚወጡ 100 ሺህ ብር፣ ለሁለተኛ 30 ሺህ እና ሶስተኛ ለሚወጡ 12 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተዘጋጅቷል።

በሁለቱም ጾታዎች ከ1ኛ እስከ 10ኛ የሚወጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚያገኙ ሲሆን በአጠቃላይ ለተወዳዳሪዎች የ306 ሺህ ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም