በሀዋሳ እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ለሸያጭ ሲያቀረቡ የተደረሰባቸው 14 ተጠርጣሪዎች ተያዙ

58

ሀዋሳ ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) በሀዋሳ ከተማ እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል ለሸያጭ ሲያቀረቡ ተደርሶባቸዋል የተባሉ 14 ተጠርጣሪዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ  የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ  ኢንስፔክተር  ግርማ  አብሽሮ  ለኢዜአ እንደተናገሩት ተጠርጣሪዎቹ ትናንት ቀን   ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ  የተያዙት በታቦር ክፍለ ከተማ ውስጥ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ  መኖሪያ ቤት በመከራየት እንጀራን ከባዕድ ነገር  ጋር በመቀላቀል  ለሸያጭ  ሲያቀርቡ እንደነበር ፖሊስ ከህዝብ በደረሰው  ጥቆማ  እንደደረሰባቸው  አስታውቀዋል።

በወቅቱ ሲያዙም ለጊዜው ምንነቱ ያልታወቀ ስድስት በርሜል ቡኮ ሊጥ አዘጋጅተው ለጋገራ አሰናድተው ነበር ብለዋል። 

በአሁኑ ወቅት የተጠርጣሪዎቹ ቤት መታሸጉንና የተቦካው ሊጥ በጤና ላይ የሚያስከትለውን  ጉዳት ለማረጋገጥ ለምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ለምርመራ መላኩን  ኢንስፔክተር  ግርማ ገልጸዋል።

ከተያዙት ተጠርጣሪዎች መካከል 12 በድርጊቱ ቀጥታ ተሳታፊ የነበሩና ቀሪዎቹ ደግሞ  ቤት አከራዮች መሆናቸውን ገልፀው ፖሊስ ምርመራ እያደረገባቸው እንደሚገኝም  አመልክተዋል።

በበዓላት  ወቅት መሰል ህገ ወጥ ተግባራትና ሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር ሊኖር ስለሚችል ህብረተሰቡ በግበይት ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኢንስፔክተሩ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም