በዓሉን ስናከብር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ በማድረግ መሆን አለበት – የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

1644

ታህሳስ 27/2013 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ የገና በዓልን ሲያከብር እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች እንዳይከሰቱ ጥንቃቄ በማድረግ መሆን እንዳለበት የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች በየዓመቱ በደማቅ ሁኔታ ከሚያከብሯቸው በዓላት አንዱ የገና በዓል ነው፡

በኢትዮጵያም በዓሉ ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ክዋኔዎች የሚከበር ሲሆን፤ በአከባበሩ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ የጥንቃቄ ጉድለቶች ምክንያት አደጋዎች ሲከሰቱ ይስተዋላል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ ያለ ባለሙያ በቤት ውስጥ የሚከናወኑ የኤሌክትሪክ ገመድ ዝርጋታዎች ለድንገተኛ የእሳት አደጋ ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ለኢዜአ የተናገሩት።

በተለይ ተጠጋግተው የተሰሩ ቤቶች ባሉባቸው መንደሮች ውስጥ ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ የሚከናወኑ የቤት ውስጥ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች ድንገተኛ የእሳት አደጋ የማስከተላቸው እድል ሰፊ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጫማሪ የማብሰያ ሲሊንደሮችን በጥንቃቄ አለመጠቀም እና እሳት ባለበት አካባቢ የቤት ውስጥ ቆሻሻ ማከማቸት ለድንገተኛ እሳት አደጋ እንደሚያጋልጥም አብራርተዋል።

በመሆኑም ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በተለይ የኤሌክትሪክ ማብሰያዎችን፤ ሲሊንደሮችን፣ ከሰል እና እንጨት እንዲሁም ሌሎች የሃይል አማራጮችን ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መጠቀም እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

የምግብ ማብሰያዎችን ከተጠቀመን በኋላ በትክክል ማጥፋታችንን ማረጋጋጥ አለብን ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከበዓል ጋር ተያይዞ ለሚከሰቱ አደጋዎች ምላሸ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል።

የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ወቅት በኮሚሽኑ በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም 011 156 86 01 እንዲሁም በነጻ የስልክ መስመር 939 በመደወል ማሳወቅ እንደሚገባም ተናግረዋል።