የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች የኦነግ ሸኔን የጥፋት ድርጊት አወገዙ

1729

ነቀምቴ 27/2013 (ኢዜአ) -የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች በሻምቡ ከተማ ባካሄዱት ሠላማዊ ሠልፍ የኦነግ ሸኔን የጥፋት ድርጊት አወገዙ።

ነዋሪዎቹ የጥፋት ቡድኑን ያወገዙት  የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት ነው።

የኦነግ ሸኔ ቡድን ከኦሮሞ ባህል ባፈነገጠ መልኩ ጭካኔ በተሞላበት ሰዎችን መግደል እንቃወማለን፣ ሀብትና ንብረት መዝረፍና ማቃጠል የዕለት ተዕለት ሥራው ያደረገው ይህ የሕወሐት ተላላኪው ቡድን የኦሮሞን ሕዝብ  አይወክልም የሚሉት ነዋሪዎቹ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል ይገኙበታል።

ቡድኑ ለዘመናት  አብረው የኖሩትን የኦሮሞንና አማራን ሕዝቦች በማጋጨት እንዲፈናቀሉ እያደረገ ያለውን ድርጊት አጥብቀው እንደሚቃወሙ ገልጸዋል ፡፡

ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በመሆን ለአካባቢያቸው ሠላም ዘብ እንደሚቆሙና በየደረጃው አደረጃጀታቸውን አጠናክረው የጥፋት ቡድኑ የገባበትን  ገብተው ለማደን ቃል ገብተዋል፡፡

ለኦነግ ሸኔ  መረጃና  ምግብ ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎች የሚያደርጉ ሴሎቻቸውን በመከታተል በህግ  ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎቹ መገልጻቸውን የዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ በቀለ ደቻሣ አስታውቀዋል፡፡

በሠላማዊ ሠልፉ ከሻምቡ ከተማና ዘጠኝ ወረዳዎች  የተውጣጡ አባ ገዳዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ወጣቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ጨምረው ገልጸዋል፡፡