በአምቦ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ከ600 በላይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአምቦ ከተማ ለችግር ለተጋለጡ ከ600 በላይ ወገኖች ድጋፍ ተደረገ

አምቦ ታህሳስ 26 /2013 (ኢዜአ) አምቦ የልጆችና የአረጋዊያን በጎ አድራጎት ድርጅት በአምቦ ከተማ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለችግር ለተጋለጡ ከ600 በላይ ወገኖች የምሳ ግብዣ እና የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
የድርጅቱ መስራችና አስተባባሪ ወጣት ኢዩኤል ከበደ እንደገጸው ድጋፉ የተደረገው በከተማው ስድስቱም ቀበሌዎች ለሚገኙ አቅመ ደካሞች፣ አረጋዊያን፣ አካል ጉዳተኞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች ነው።
ከምሳው ግብዣ በተጨማሪ 200 ለሚሆኑ ወላጆቻቸወን ላጡና ችግረኛ ህጻናት የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን ተናግሯል፡፡
ድርጅቱ 38 ረዳት የሌላቸው አረጋዊያንና ህጻናትን ተቀብሎ እያስተዳደረ እንደሚገኝም ተመልክቷል፡፡
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አሸናፊ አጀማ በበኩላቸው ወጣቱ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ያደረገውን ድጋፍ አድንቀው ሌሎችም ይህንን አርአያነት እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ እገዛም እንደማይለያቸው አስታውቀዋል፡፡
የአምቦ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ሙሉነሽ ነጋሳ ድርጅቱ ችግረኞችን ከጎዳና ላይ አስነስቶ ድጋፍ በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ድርጅቱ በቅርብ ጊዜ የተቋቋመ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ስራ እያከናወናቸው ያሉት ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ድጋፍ ከተደረገላቸው መካከል ወጣት ኤሊያስ ሰሙ ንጉስ በሰጠው አስተያየት ድርጅቱ
በዓሉን ምክንያት በማድረግ ባደረገልን የምሳ ግብዣ አመሰግናለሁ ብሏል።
መንግስትም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው እንደሚፈልግም ገልጿል።
የአምስተኛ ክፍለ ተማሪ ሂሩት መንግስቱ ለተደረገላት የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አመስግና ሌሎች እንደእርሷ የተቸገሩ ብዙ ስላሉ ለነሱም ቢደረግ ደስ ይለኛል ብላለች፡፡