የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጠንካራ እንዲሆን ገለልተኛ ሆኖ ሊደራጅ እንደሚገባ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጠንካራ እንዲሆን ገለልተኛ ሆኖ ሊደራጅ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጠንካራ ሆኖ የንግዱን ማህበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዲችል ገለልተኛ ሆኖ ሊደራጅ እንደሚገባ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን አስመልክቶ በሥራ ላይ የነበረውን አዋጅ ለማሻሻል የሚረዳ ግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የቀድሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት የሥራ አመራሮች ተገኝተዋል።
አዲስ ተሻሽሎ የሚወጣው አዋጅ ምን ምን ጉዳዮችን ማካተት አለበት? እንዴት ጠንካራ የምክር ቤት አደረጃጀት መፍጠር ያሻል የሚሉት ጉዳዮችም በውይይቱ ትኩረት የተደረገባቸው ናቸው።
ዘርፉ የሚመራበት አዋጅ 341/95 ላለፉት ዓመታት ሥራ ላይ ቢውልም የንግዱ ማህበረሰብን ችግሮች በሚጠበቀው ደረጃ አለመፍታቱን በዚሁ ወቅት ተነስቷል።
ይልቁንም ባለፉት18 ዓመታት አዋጁ የውዝግብ መነሻ ሆኖ መቆየቱን ነው በመድረኩ የተጠቀሰው።
በንግድ ሚኒስቴር የተዘጋጀው አዲስ የተሻሻለው አዋጅ በግብአት እንዲዳብር መደረጉ ችግሩን ለመፍታት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው በመድረኩ ተሳታፊዎች የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በዚሁ ወቅት እንደተናገሩ የቀድሞው አዋጅ የምክር ቤት አባልነት አስገዳጅ አልነበረም።
በዚህም ምክር ቤቶች ራሳቸውን ለማደራጀትና በገቢም ራሳቸውን ለመቻል ይቸገሩ ነበር።
ከዚህ ቀደም የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ራሳቸውን የቻለ አደረጃጀት እንደነበራቸው አስታውሰው፣ ይህም አቀናጅቶ ለመምራት ማስቸገሩንና የልዩነት መንስኤ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
እንደ ኢንጂነር መላኩ ገለጻ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት የንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በሚል የሚደራጁ ሲሆን ይህም የንግዱን ማህበረሰብ ወደ አንድ በማምጣት ጠንካራ አደረጃጀት ለመፍጠርና ችግሮቻቸውን ለመፍታት ያግዛል።
"የንግዱ ማህበረሰብ መደራጀት መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ጠንካራ እንዲሆኑም ያግዛል" ብለዋል።
"የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ከተጽእኖ ነጻ ሆኖ እንዲደራጅ በማድረግ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር ይገባል" ያሉት ደግሞ የቀድሞ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃነ መዋ ናቸው።
"ከመንግስት ጋር የሚለጠፉ ነጋዴዎች የንግዱን ማህበረሰብ ችግር የሚፈቱ አይደለም" ያሉት አቶ ብርሃነ፣ ለህብረተሰቡ የሚቆምና የንግዱን ማህበረሰብ ችግር የሚፈታ ጠንካራ ተቋም መፍጠር እንደሚገባም አመልክተዋል።
"ንግድ ምክር ቤቶች የሚጠበቀቅባቸውን ሥራ ለማከናወን በቅድሚያ የራሳቸውን አቅም ሊገነቡ ይገባል" ያሉት ደግሞ ሌላው የቀድሞ የምክር ቤቱ አባል አቶ ክቡር ገና ናቸው።
የአንዳንድ አገራት ንግድ ምክር ቤቶች በስልጠና፣ በማስተማርና የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፣ የተሻለ አደረጃጀት ለመፍጠር ልምድ መቅሰም እንደሚገባም አክለዋል።