የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ለመተከል ዞን ተፈናቃዮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ወሰኑ

63

አሶሳ ታህሳስ 26 /2013 (ኢዜአ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ለመተከል ዞን ተፈናቃዮች ድጋፍ እንዲወል የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለመስጠት መወሰናቸው ተገለጸ።

አመራሮቹ ድጋፉን ለመስጠት የወሰኑት በአሶሳ ከተማ ባካሄዱት የውይይት መድረክ ላይ  ነው።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባክር ከሊፋ በወቅቱ   እንደተናገሩት  በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው ኮማንድ ፖስት የመተከልን ሠላም ለመመለስ ሃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ ነው፡፡

ኮማንድ ፖስቱ መተከልን ከተቆጣጠር በኋላ የዞኑ ሠላም እየተረጋጋ ነው ብለዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ህብረተሱም በዞኑ የጥፋት ሃይሎችን በማጋለጥ ያለስጋት ለጸጥታ ሃይሉ ጥቆማ መስጠት መጀመሩን  ገልጸዋል፡፡

የመተከል ሠላም በቅርቡ ሙሉ ለሙሉ ይመለሳል ያሉት  አቶ ባበክር የክልሉ መንግስት በዚህ ወሳኝ ወቅት ለተፈናቃዮች ድጋፍ እያሰባሰበ መሆኑን አሰታውቀዋል፡፡

የወር ደመወዛቸውን ለመስጠት ከወሰኑ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮቹ መካከል አቶ ሃብታሙ አለነ መሰል የህዝብ ጉዳቶች በሚያጋጥሙበት ወቅት የሕይወት መስዋእትነት ጭምር መክፈል እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ በዘላቂነት እስኪቋቋም የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በጸጥታ ችግር ወቅት የመረጃ አያያዛችንን ማስተካከል አለብን ያሉት አቶ ሃብታሙ ይህም ለመልሶ ማቋቋም ስራው ወሳኝ እንደሆነ አስተረድዋል፡፡

ወይዘሮ ሂጂራ ኢብራሂም በበኩላቸው  በክልሉ የሚገኙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለመተከል ተፈናቃዮች እያቀረቡ የሚገኘውን ድጋፍ ግለሰቦች የራሳቸው በማስመሰል እውቅና ለማግኘት እየጣሩ በመሆኑ ሊስተካል ይገባል ብለዋል፡፡

እንዲሁም ለተፈናቃዮች የመጡ ድጋፎች በመጋዘን ተከማችተው ከማስቀመጥ ይልቅ ፈጥነው ለህብረተሰቡ መድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡

የመተከል የጸጥታ ችግር ከአካባቢው  ማህበረሰብ የወጣ በጁንታው የሚመራ ጥቂት ሽፍታ የፈጸመው ጥፋት  እንደሆነ የተናገሩት ደግሞ አቶ ዘላለም ጃለታ ናቸው፡፡

በጥቃቱ የአካባቢው ማህብረሰብም  ተጎጂ መሆኑን ጠቅሰው አሁንም የዞኑን ህዝብ ስጋት ውስጥ ለመክተት  የሃሰት ወሬ እየተነዛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሽፍታውን ፕሮፓጋንዳ ብዥታ የሚያጠራ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙዩኒኬሽን  ስራ እንደሚያስፈልግ አቶ ዘላለም የጠቆሙት፡፡

ይህም በጸጥታው ችግር ሸሽተው ወደ ጫካ የገቡ የማህበረሰብ ክፍሎችን ማሰባሰብ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም