ገቢዎች ሚኒስቴር በወላይታ ሶዶ በእሳት ቃጠሎ ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ገቢዎች ሚኒስቴር በወላይታ ሶዶ በእሳት ቃጠሎ ለተጎዱ ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች አበረከተ

ሶዶ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) ገቢዎች ሚኒስቴር በወላይታ ሶዶ ከተማ ንብረታቸው በእሳት ቃጠሎ ለወደመባቸው ወገኖች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ቁሳቁሶች አበረከተ።
በገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው የሚመራ የጉምሩክ ኮሚሽንና ብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች ሉኡካን ዛሬ በወላይታ ሶዶ ቃጠሎ የደረሰበትን የመርካቶ ገበያ ሥፍራ ተመልክተዋል።
ሚኒስትሩ በወቅቱ እንዳሉት ቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰና በገበያ ስፍራው በሚገኝ የገቢ ምንጭ የሚተዳደሩ በርካታ ወገኖችን ለችግር የዳረገ ነው።
እነዚህን ወገኖች ለማቋቋም እየተደረገ ያለው ርብርብ የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለመደ የመረዳዳትና የመደጋገፍ በጎነቱን ለእነዚህ ወገኖች ሊያሳዩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሚንስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ብርድ ልብስ፣ ልዩ ልዩ አልባሳትና ጫማዎችን መለገሱን አስታውቀዋል።
ወደፊትም ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ አስፈላጊው ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አቶ ላቀ አስታውቀዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር እንድርያስ ጌታ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቃጠሎው ንብረታቸው የወደመባቸውን አካላት ለመደጋፍ እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
የዞኑ አስተዳደር ተጎጂዎችን ለማቋቋም ኮሚቴ አዋቅሮ ገቢ ለማሰባሰብ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የገቢዎች ሚኒስትር ያበረከተውን ድጋፍ ለተጎጂዎቹ በፍትሀዊነት እንደሚከፋፈል ገልጸዋል።