በወንጀል በተጠረጠሩ 10 የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ ፖሊስ የ14 ሰዎችን የምስክርነት ቃል ተቀበለ

1737

አዲስ አበባ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) ከሕወሃት የጥፋት ቡድን ተልዕኮ በመቀበል በወንጀል ድርጊት በተጠረጠሩ አስር የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮች ላይ መርማሪ ፖሊስ የ14 ሰዎችን የምስክርነት ቃል መቀበሉን ገለፀ።

የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ከህወሃት ጁንታ ተልዕኮ በመቀበል በወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩ 10 የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አመራሮችን ጉዳይ ተመልክቷል።

በዚህ መዝገብ ኮሎኔል ሃረጎት በርሄ፤ ሌተናል ኮሎኔል ሙሉ አለሙ፤ ብርጋዴል ጄነራል ይልማ ከበደ፤ ኮሎኔል በረከት ወልደአብየዝጊ፤ ሌቴናል ኮሎኔል ግደይ ገብረየሱስ፤ ሻለቃ ሃሳቡ መሃመድ፤ መቶ አለቃ ጸሃየ ሃይሉ፤ ኮሎኔል ይርጋለም ፍቃዱ ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹ ለሕውሃት የጥፋት ቡድን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠታቸውንና በመንግስት በጀትም በድብቅ ለትግራይ ልዩ ሃይል ስልጠና ሲሰጡ እንደነበር ፖሊስ ማስረጃ አግኝቻለሁ ብሏል።

እስካሁን የተጠርጣሪዎችን ቃል የመቀበል ስራ የተከናወነ ሲሆን በኤርፖርት የደረሰውንም  የጉዳት መጠን መረጃ ማምጣቱንም አስታውቋል።

በውጭ ሀገር ላሉ የጥፋት ተላላኪዎች ሃሰተኛ መረጃ በማቀበል ጭምር በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን ለመፈፀም መንቀሳቀሳቸውንም ፖሊስ አረጋግጫለሁ ብሏል።

በተጨማሪም ቀሪ የምርመራ ስራ ለማከናወንና የተለያዩ የቴክኒክ፣ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ለማሰባሰብ 14 ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው ”መርማሪ ፖሊስ የወንጀል ተሳትፏችንን ለይቶ ሊያቀርብ ይገባል፣ በጉዳዩ ላይ የሁላችንም ተጠያቂነትና የወንጀል ተጠርጣሪነት ተመሳሳይ ሆኖ መቅረብ የለበትም ” ሲሉ ተከራክረዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት 11 ቀን በመፍቀድ ለጥር 6 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።