ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በሜጀር ጀኔራል ከድር አራርሶ ላይ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ

1610

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሜጀር ጀኔራል ከድር አራርሶ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ለመፍቀድ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

የሰሜን ዕዝ ሎጂስቲክ ኃላፊ የነበሩት ሜጀር ጀኔራል ከድር አራርሶ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ቀርበዋል።

ተጠርጣሪው የሰሜን ዕዝ ምክትል አዛዥና የሎጂስቲክስ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ ከሕወሃትና ኦነግ ሸኔ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት የአገር ክህደት ወንጀል በመፈፀም ተጠርጥረው ፍርድ ቤት መቅረባቸው የሚታወቅ ነው።

ተጠርጣሪው መንግስት በትግራይ ክልል የነበረ የጦር መሳሪያ ወደ መሐል አገር እንዲመጣ ሲፈልግ መሳሪያው ከመቀሌ እንዳይወጣ ሲቃወሙ እንደነበርም መግለጹ የሚታወቅ ነው።

የአገር መከላከያ ሰራዊት የጦር መሳሪያ በትግራይ ክልል የት እንደሚገኝ መረጃ በመስጠትና እንዲዘረፍ በማድረግ ሲንቀሳቀሱ እንደነበርም አመልክቷል።

በቀጣይም የምስክር ቃል መቀበል፣ የቴክኒክ ማስረጃዎችን የማምጣት፣ መረጃዎችን የማደራጀትና በትግራይ ክልል የወደሙ ንብረቶችን ለመለየት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜው እንዲፈቀድለት መርማሪ ፖሊስ ጠይቋል።

በተጨማሪም ያልተያዙ ግብረ-አበሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የምርመራ ጊዜው እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው በበኩላቸው ”ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኘኝ ጉዳይ የለም መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ ቀናት ሊፈቀድለት አይገባም” ሲሉ ተከራክረዋል።

የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ በጠየቀው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ላይ ውሳኔ ለመስጠትም ለታህሳስ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።