ኤጀንሲው በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች የስጋ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ዝግጅት መደረጉን ገለጸ

77

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመጪው የገና በዓል በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች የስጋ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ስራ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው መጪውን የገና እና የጥምቀት በዓላት አስመልክቶ ከሸማቾች ህብረት ማህበራት አመራሮችና ከ200 በላይ ከሚሆኑ የልኳንዳ ቤት ባለቤቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብነህ እምሩ በመጪው የገና በዓል በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች የስጋ አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ከህብረት ስራ ዩኒየኖች ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዩኒየኖች አማካኝነት የእርድ ሰንጋዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለልኳንዳ ቤቶች እንደሚቀርብም ነው የገለጹት።

በኤጀንሲው የግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ደብሪቱ ለዓለም በበኩላቸው ልኳንዳ ቤቶቹ ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በበዓል ጊዜ የሚፈጠርን መጨናነቅ ለመቀነስም ቅድመ ስራዎች ከመደበኛ ሰዓት ውጪ እንደሚከናወኑ ገልጸዋል።

ልኳንዳ ቤቶች ለሰራተኞቻቸው በቂ የኮሮናቫይረስ ጥንቃቄ ግብዓት እንዲያዘጋጁ መደረጉንም ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ወደ ልኳንዳ ቤቶች በሚመጣበት ጊዜ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀምን ጨምሮ ሌሎች የጥንቃቄ መመሪያዎችን ተግባራዊ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የልኳንዳ ቤት ባለቤቶች በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ለእርድ የሚቀርቡላቸው በሬዎች ዋጋ ውድ በመሆኑ የስጋ ዋጋ ተመን ተመጣጣኝ እንዳልነበር አስታውሰዋል።

በህብረት ስራ ዩኒየኖች በኩል የእርድ በሬዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርቡ መደረጉ ልኳንዳ ቤቶች በወጣው ተመን እንዲሸጡ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም