በጋምቤላ ክልል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የትራፊክ አደጋን የመከላከሉ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ

1643

ጋምቤላ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል የህብረተሰቡ ግንዛቤ በማሳደግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የትራፊክ አደጋን የመከላከሉ ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ ተመለከተ።

’’ከጳጉሜ እስክ ጳጉሜ እንደረሳለን’’  መሪ ሀሳብ  እየተካሄደ ያለው  አራተኛው ዙር  የእግረኞችና ብስክሌተኞች ቀን  ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።

የጋምቤላ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ኤርሚያስ ወልደሰማያት በወቅቱ እንዳሉት  ቀደም ሲል ግፊትን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ከቅንጦታዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተይይዙ በስፋት የሚከሰቱት በአደጉ ሀገራት ነበር።

’’አሁን ላይ ሀገራችን ጨምሮ በሌሎች በማደግ ላይ በሚገኙ ሀገራት ጭምር የደም ግፍት፣ ስኳርና ሌሎች ተላለፊ ያልሆኑ በሽታዎች ቀዳሚ የጤና ችግር እየሆኑ መጥተዋል’’  ብለዋል።

በጋምቤላ ክልልም በእነዚሁ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየተጠቁ ያሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይም በክትትል ማነስ በሽታዎች መያዛቸውን ሳያውቁት ህይወታቸው የሚያልፍ  ሰዎች ቁጥር ቀላል አንዳልሆነ ተናግረዋል።

አሁን ላይ በየወሩ መጨረሻ እየተካሄደ ያለው ነፃ የደም ግፊትና ስኳር ምርመራ  ህብረተሰቡን  አስቀድሞ እራሱን በማወቅ  ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች  እንዲጠበቅ  ምቹ ሁኔታን  እንደሚፈጥርለት  ዶክተር ኤርሚያስ ገልጸዋል።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የትራንሰፖርት ፖሊሲ  ጥናት ባለሙያ አቶ የሻነው ውዴ  በበኩላቸው ፤ መስሪያ ቤታቸው በሀገሪቱ እየተበራከተ የመጣውን  የትራፊክ አደጋ  ለመቀነስ  ሞተር አልባ የትራንፖርት ስትራቴጂ ቀርፆ እየሰራ ነው ብለዋል።

ስትራቴጂው በተለይም ህብረተሰቡ በእግርና ብስክሌት  በመጓዝ ለትራፊክ  አደጋ  የመጋለጥ  አጋጠሚውን ከመቀነስ  ባለፈ በአካላዊ እንቅስቃሴ ችግር  ሊከሰቱ የሚችሉ  በሽታዎችን  በመከላከል በኩልም የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ሚኒስቴሩ ጋምቤላን ጨምሮ ከሌሎች የክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት  ’’ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ እንደርሳለን’’ መሪ ሃሰብ የመተግበርና የማስረጽ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል።

የክልሉ ትርንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደፋር ተሬሳ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ እየተበራከተ የመጣን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ቢሮው ከሚኒስቴሩ ጋር በቅንጅት  እየሰራ  ነው ብለዋል።

ካለፈው ጳጉሜ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የንቅናቄ መድረክ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተከናወነ የሚገኘው ስራ አካል መሆኑም ገልጸዋል።

በጋምቤላ ከተማ ባለፉት 37 ዓመታት ብስክሌት  በማሽከርከር ምስጉን የሆኑት  65 ዓመት እድሜ ያላቸው አቶ ለገሰ ተርፋ ብስክሌት   በማሽከረከራቸው  ሙሉ ጤናማ  መሆናቸውንና  ምንም ዓይነት የህመም  ስሜት እንደሌላቸው ተሞክሯችውን አካፈለዋል።

በእድሜያቸው አንዴ ከገጠማቸው የትራፊክ አደጋ ሌላ የጤና እክል ገጥማቸው እንዳማያውቅ  ገልጸው የእግርና ብስክሌት  ጉዞ በማድረግ ጤናን  መጠበቅ እንደሚችል ከራሳቸው ተሞክሮ መረጋጋጥ እንደቻሉ ገልጸዋል።

በዝግጅቱ የእግርና የብስክሌት ጉዞ እንዲሁም ነፃ የደም  ግፊትና የስኳር  ምርመራ  ተካሂዷል።