በአዲስ አበባ ባለፉት አምስት ወራት 141 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል አግኝተዋል - የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ

87

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26 ቀን 2013 (ኢዜአ) ባለፉት አምስት ወራት በአዲስ አበባ ለሚገኙ 141 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን የከተማ አስተዳደሩ የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ገለጸ።

ከመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ 880 ወጣቶች በአገራዊ ብልጽግና ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የወጣቶችና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊው አቶ አብርሃም ታደሰ እንደገለጹት፤ የመዲናዋን ወጣቶች ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

እንደ ሃላፊው ገለፃ፤ በዚህ ዓመት ለ280 ሺህ ወጣቶች ስራ ለመፍጠር ታቅዶ 141 ሺህ ያህል ወጣቶች ሥራ አግኝተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ 200 ሚሊዮን ብር በመመደብ 28 ሺህ ወጣቶችን በአረንጓዴ ልማት ለማሳተፍ ስልጠና እየሰጠ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በኩል 2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱን ጠቅሰው 300 ሚሊዮን ብር በሊዝ ፋይናንሲንግ በመመደብ የከተማዋን ወጣቶች ለመጥቀም መታቀዱንም አብራርተዋል።

በተለያዩ የስራ መስኮች ተደራጅተው ለሚንቀሳቀሱ ወጣቶች 5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገበያ ትስስር እንደሚፈጠር ተናግረዋል።በፖለቲካ ተሳትፎ የአስፈጻሚ ወጣቶች ምጣኔ 70 በመቶ መድረሱንና ይህንንም ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

የመዲናዋ ወጣቶች በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ከሚከውኗቸው ተግባራት መካከል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቀዳሚ ነው።

በአዲስ አበባ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል በተደራጀ መልኩ የሚንቀሳቀሱት ከ25 በመቶ በታች እንደሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም