በማዕከላዊ ጎንደር በተለያየ ሰብል ከለማው ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት አብዛኛው ምርት ተሰበሰበ

1694

ጎንደር/ነገሌ/ ኢዜአ ታህሳስ 26/2013 በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመኸሩ ወቅት ከለማው ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 92 በመቶው ምርት ለብክነት ሳይጋለጥ መሰብሰብ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። 

በተመሳሳይ በኦሮሚያ  ጉጂ ዞንም ከሚጠበቀው ምርት እስካሁን ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ መሰብሰቡ ተመልክቷል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ ዮሃንስ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ በዞኑ  500 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያየ ሰብል  ለምቷል።

ከለማው መሬት ውስጥም 474 ሺህ ሄክታሩ የምርት ብክነት ሳይደርስ ወቅቱን ጠብቆ መሰብሰብ እንደተቻለ አስታውቀዋል።

አርሶአደሩ ባህላዊ የደቦ ሰብል ስብስባን ጨምሮ ቤተሰቡን ባሳተፈ መንገድ የደረሰ ሰብልን በወቅቱ እንዲሰበሰብ ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሩ እስከ ጥርና የካቲት ድረስ የሚዘልቀው ሰብል የመሰብሰብ ልማዳዊ አሰራር ለምርት ጥራት መጓደልና ለብክነትም የሚያጋልጥ መሆኑን በማስተማርና በመቀስቀስ ለውጥ እንዲያመጣ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለዘመናት የዘለቀውን የአርሶ አደሩን ኋላቀር የሰብል አመራረት ዘዴ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረትም ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም እርሻ እንዲሁም 256ሺ ሄክታር መሬት ደግሞ በመስመር እንዲለማ ተደርጓል ብለዋል፡፡

በምርት ዘመኑ ገበያ ተኮር የሆኑ ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ የቢራ ገብስ፣ ስንዴና በቆሎ በስፋት አርሶ አደሩ እንዲያለማቸው መደረጉንም አስረድተዋል፡፡

በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ቀበሌ አርሶ አደር ቢሰጥ መልኬ በሰጡት አስተያየት  ዝናብ በወቅቱና በበቂ መጠን በማግኘታቸው የዘሩት ጤፍና ዳጉሳ በጊዜው  አጭደው መሰብሰብ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ሌላው የዚሁ ወረዳ  አርሶ አደር አለኸኝ መኮንን በበኩላቸው ሰብል በወቅቱ መሰብሰብ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ በውል በመገንዘቤ የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ እስኪወቃ ደረስ በተገቢው መንገድ ከምሬ አስቀምጫለሁ ብለዋል፡፡

ሰብሉ በሚገባ አልደረቀም በሚል በማሳ ላይ ረጅም ቀናት ሳይታጨድ የሚቆየው ሰብል በዝናብና ንፋስ እንዲሁም በእንስሳት ጭምር በሚደርስበት ጉዳት ለምርት ብክነት ያጋልጠን ነበር ሲሉም አስረድተዋል፡፡  

በዞኑ በተለያየ ሰብል ከለማው አጠቃላይ  መሬት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ጉጂ ዞን በመኸር ወቅት ከለማው መሬት እስካሁን ከ700 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ገልጿል፡፡


በጽህፈት ቤቱ የሰብል ልማት ባለሙያ ወይዘሮ እናት አሰፋ በጉጂ ዞን በወቅቱ ከ176 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዓይነት መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

በገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍና ቦለቄ ዘር ከተሸፈነው ከዚሁ መሬት ሶስት ሚሊዮን 900ሺህ  ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል፡፡

እስካሁን ከዚህ ውስጥ የደረሰ 730 ሺህ 100 ኩንታል ምርት በአርሶ አደሩ መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች ባልተለመደ መልኩ ሰሞኑን የሚታየው ደመና ጋር ተያይዞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና በአንበጣ ሊደርስ በሚችል  ጉዳት  ምክንያት መጠነኛ የምርት መቀነስ ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያዋ እንዳሉት የአርሶ አደሩን ግንዛቤ በማሳደግ ብክነቱን ለመከላከል በአንድ ሺህ የልማት ጣቢያ ሰራተኞች በምርት አሰባሰብ ላይ ያተኮረ ሙያዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው።

በዞኑ የአናሶራ ወረዳ ነዋሪ አቶ እያሱ ሾንቃ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በጥራጥሬ ሰብል ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ተናግረዋል፡፡

ሆኖም ለደረሰ ሰብል ቅድሚያ ሰጥተው በመሰብሰብ ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለማምለጥ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገመዳ ሶራ ዓመቱን ሙሉ የደከሙበት ሰብል በአብዛኛው ባለመሰብሰቡ እንደሚያሰጋቸው ተናግረዋል፡፡

“የጤፍ ስንዴና የጥራጥሬ ሰብል በቀላሉ የሚበላሹና ወቅቱን ላልጠበቀ ዝናብ ተጋላጭ በመሆኑ ከጉዳት ለመታደግ በትኩረት እየሰበሰብን ነው” ብለዋል፡፡