የጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ህዝብን ሠላምና አብሮነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለጸ

77

ጋምቤላ፣ ታህሳስ 26/2013 (ኢዜአ) የጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች ህዝቦች ሠላም፣ አንድነትና አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰራ ተገለጸ።

የሁለቱ ክልሎች የአዋሳኝ ዞኖች የሠላምና ጸጥታ የጋራ የውይይት መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መተተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የውይይት መድረኩን ሲከፍቱ የህወሓት የጥፋት ቡድን የተጀመረውን የለውጥና ብልጽግና ጉዞ ለማደናቀፍ ህዝቦችን በዘር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ በመከፋፈል ሲያጋጭ መቆየቱን አስታውሰዋል።

የህዝቦችን አንድነትና አብሮነት ለመሸርሸር በጥፋት ኃይሎች የሚደረገውን ሴራ በማምከን አገራዊ ለውጡን ወደፊት ለማሻገር አመራሮቹ በትጋት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

በጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ዞኖች የሚኖሩ ህዝቦችን ሠላምና ልማት ለማጠናከር የተዋሳኝ ዞኖች አመራሮች ጠንክረው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጅብሪል ሙሐመድ በበኩላቸው የጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች ህዝቦች የቆየ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ያላቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል።

ይህንን የቆየ አብሮነትና ወንድማማችነት ለመናድ ባለፉት ዓመታት እኩይ ዓላማ ያላቸው ሀይሎች ያልተቆጠበ ጥረት ቢያደረጉም በህዝቦች የጋራ ጥረት ማክሸፍ መቻሉን ገልጸዋል።

አንድነትና አብሮነቱ ተጠናከሮ እንዲቀጥል የሚሰራ መሆኑን አቶ ጅብሪል አረጋግጠዋል።

በተዋሳኝ ዞኖቹ የተጀመረው የጋራ ምክክር መድረክ የሠላም፣ ጸጥታና የልማት ስራዎችን በማጠናከር ለውጡን ወደፊት ለማራመድ እንዲያግዝ የተዘጋጀ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃለፊ አቶ ቶማስ ቱት ናቸው።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ምክክር መድረክ የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ አካላት፣ የተወሳኝ ዞኖች አመራሮች፣ የአገር መከላከያና የፌዴራል ፖሊስ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም