በህግ ማስከበር እርምጃው የሚጠበቅብንን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን- የመተከል ዞን የሀገር ሽማግሌዎች

103

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 26/2013 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን መንግስት ወንጀለኞችን አድኖ ለሀግ ለማቅረብ እያከናወነ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።

በፌዴራሉ መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል ከመተከል ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ከተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ውይይት አካሄዷል።

የመተከል ዞን በርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በጋራ የሚኖሩበት ሲሆን በማህበረሰቡ ዘንድ መተሳሰቡና አብሮነቱ መኖሩንም የሀገር ሽማግሌዎቹ አንስተዋል።

ሆኖም ዞኑ ከሚታወቅበት የአብሮነት እሴት ባፈነገጠ መልኩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙ እጅግ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ የጉሙዝን ብሔረሰብ የማይወክሉ 'የተደራጁ ሽፍቶች' መሆናቸውን ጠቅሰው፤ እነዚህ ሽፍቶች ችግሩ እንዳይከሰት ሲጥሩ በነበሩ የሀገር ሽማግሌዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውንም ተናግረዋል።

በጉሙዝ ማህበረሰብ ግጭትን በመፍታት ረገድ ትልቅ ሚና ባላቸው እናቶች ላይ ጭምር ጉዳት ማድረሳቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።   

በእርሻ ኢንቨስትመንት ስም በአካባቢው የተሰማሩ የጽንፈኛው የህወሃት ጁንታ አባላቶች ወጣቶችን ሰብስበው ለጥፋት ተልኮ ሲያሰለጥኑ እንደነበርም ነው የሀገር ሽማግሌዎቹ የተናገሩት።

ይህንን እያወቁ ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጡ አመራሮች መኖራቸውንም አንስተዋል።

በመሆኑም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ አመራሮች ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቀዋል።

በጥቃቱ እጃቸው ያለበትን ማናቸውንም አካል ለህግ በማቅረብ አካባቢውን ወደ ሰላምና መረጋጋት የመመለስ ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራም የሀገር ሽማግሌዎቹ ጠይቀዋል።

መንግስት በዞኑ እያከናወነ ባለው የህግ ማስከበር እርምጃ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም የሀገር ሽማግሌዎቹ አረጋግጠዋል።

በዞኑ በተቋቋመው ግብረ ሃይል የህግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ በበላይነት የሚመሩት ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ

አመራሮች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በዞኑ የተከሰተው ችግር ከመንግስት አቅም በላይ አለመሆኑንም ገልጸዋል።

በጥፋት ቡድኑ አባላቶች ላይ ከሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ጎን ለጎን በህብረተሰቡ ውስጥ የተሰገሰጉ የጥፋት ሃይሉ አባላቶችን ለይቶ የማጥራት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሀገር ሽማግሌዎች መንግስት በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን እያከነወነ ያለውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበው፤ ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም