በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን እንደሚያስቀጥሉ የአሮሞና አማራ ተወላጆች ገለጹ

63

ነቀምቴ፣ ታህሣሥ 26/2013 (ኢዜአ) ተከባብረው በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን እንደሚያስቀጥሉ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የሚኖሩ የኦሮሞና አማራ ተወላጆች ገለጹ። 

ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ከሚገኙ ቀበሌዎች የተውጣጡ  የኦሮሞና አማራ ተወላጆች የተሳተፉበት የሠላምና ልማት ኮንፍረንስ በጉቶ ጊዳ ወረዳ ማዕከል ተካሂዷል።

ከኮንፍረንሱ ተሳታፊዎች መካከል በየጉደ ያቢላ ወረዳ የአባይ ዳሌ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ወርቁ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የሁለቱ ህዝቦችን ወንድማማችነትን፣ መቻቻልን፣ መከባበርንና መደጋገፍን በማጠናከር በሠላም አብሮ የመኖር እሴቶቻቸውን ለማስቀጠል የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

በሲቡ ስሬ ወረዳ የበቆ ጅማ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታምራት አቻምየለህ በበኩላቸው በአማራና ኦሮሞ መካከል  የኖረውን ሠላም፣ ልማትና ትስስርን  ለማጠናከር የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

የህዝቦችን  ሠላም በማወክ የሰውን ህይወት ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በጋራ ለመከላከልና አጋልጠውም ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሰሩ አመልክተዋል፡፡

ሁለቱን ህዝቦች በማጋጨት ሕይወት በከንቱ እንዲጠፋ የሚያደርጉ የህወሐት ጁንታ ተላላኪው  ኦነግ ሸኔን በጋራ አጋልጠውም ለሕግ ለማቅረብ መዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ በጉቶ ጊዳ ወረዳ የሉጎ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ታደሰ ጉደታ ናቸው።

ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አበበ ታደሰ ሁለቱ ሕዝቦች ተጋብተው የተዋለዱ በመሆናቸው የትኛውም ኃይል ሊለያቸው እንደማይችል ገልጸዋል።

በገዳ ሥርዓት የኦሮሞ ህዝብ አግላይ ሳይሆን አቃፊ በመሆኑ በአካባቢያቸው ካሉ የአማራ ተወላጆች ጋር ከምንጊዜውም በላይ አንድነታቸውን አጠናክረው በሠላም አብረው የመኖር እሴቶቻቸውን  እንደሚያስቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ዴሬሳ ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የኖሩ  መሆናቸውን አስታውሰዋል።

ኦነግ ሸኔ ሁለቱን ህዝቦች ለማጋጨት የሚነዙትን አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ጠንቅቀው በመረዳት አንድነታቸውን በማጠናከር  አጥፊዎቹን አጋልጠው ለሕግ ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በኮንፍረንሱ ከሁለቱም ተወላጆች የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና አመራሮችና  የፀጥታ አካላት መሳተፋቸውን  ሪፖርተራችን ከስፍራው ዘገቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም