በክልሉ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ዛሬ ተጀመረ

1861

አሶሳ፣ ታህሳስ 26 / 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የስምንተኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ዛሬ መሰጠት ተጀመረ፡፡ 

በክልሉ ትምህርት ቢሮ የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት አቅርቦትና ትግበራ ዳይሬክተር አቶ ግርማ አሰጌ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ ፈተናው እየተሰጠ ያለው በ210 ትምህርት ቤቶች ነው።

ፈተናውን 15 ሺህ 770 ተማሪዎች እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።

“ፈተናው የጸጥታ ስጋት ባለበት መተከል ዞን በስድስት ወረዳዎችና በአንድ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ 97 ትምህርት ቤቶች ለጊዜው እንዲራዘም የቢሮው ማኔጅመንት ወስኗል” ብለዋል፡፡

ቢሮው የዞኑ ጸጥታ ሲረጋጋ ከሃገር አቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ጋር በመቀናጀት ፈተናውን ለመስጠት መታቀዱን አመልክተዋል፡፡

ፈተናው እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚሰጥ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።