በአማራ ክልል ሴቶችን በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ ውጤታማ ስራ ተከናውኗል- የፌዴራል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ

90

ባህር ዳር፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ)  በአማራ ክልል ሴቶችን በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወነ ያለው ስራ ሌሎች ክልሎች ተሞክሮውን ወስደው ሊያሰፉት እንደሚገባ የፌዴራል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አስገነዘበ። 

ከፌዴራልና ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሊጉ ከፍተኛ አመራሮች በባህር ዳርና ደቡብ ጎንደር ዞን በአባላቱ የተሰሩ ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የፌዴራል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ ዛሬ በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የማጠቃለያ ውይይት ላይ እንደገለጹት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

በአማራ ክልል ባህርዳርና በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ የሴቶች ሊግ አባላትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተሰራው ስራ ውጤታማ መሆኑን በአካል ተገኝተው ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል።

"በተለይ በዶሮ እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ተደራጅተው ወደ ስራ የገቡ ሴቶች ራሳቸውን ከመቻል አልፈው ለሌሎች ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው" ብለዋል።

ሴቶች  ተተኪ አመራር ለማፍራት እያከናወኑ ባሉት ስራ አቅምና ብቃት ያላቸው አባላት ታች ድረስ መኖራቸውን ማረጋገጥ እንደቻሉም ጠቅሰዋል።

በመስክ ጉብኝቱ የተገኘውን ምርጥ ተሞክሮ ከየክልሉ የመጡ የሊጉ ከፍተኛ አመራሮች ወስደው በማስፋት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሊሰሩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቷ አስገንዘበዋል።

የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መሰሉ ብርሃኑ በበኩላቸው የክልሉን ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የሊጉን አባላት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተለዩ 88 ሺህ ሴቶች ውስጥ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 13 ሺህ ለሚሆኑት በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው መሆኑን ጠቀሰዋል።

"በግብርና፣ በመስኖ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በዶሮ እርባታ፣ በጨርቃጨርቅና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች የተሰማሩ አባላት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል" ብለዋል።

ቀደም ሲል የተጀመሩ ስራዎችም በእውቀትና ልምድ ዳብረው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመላክተዋል።

የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በአማራ ክልል የተሰራው ስራ ውጤታማ ሆኖ ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ የጉብኝቱ ተሳታፊና የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ነኢማ ሙኒር ናቸው።

በመስክ ጉብኝት ያዩትን ምርጥ ተሞክሮ ወደ ክልላቸው ወስደው በማስፋትና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩ አረጋገጠዋል።

ሌላዋ የጉብኝቱ ተሳታፊ የጋምቤላ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አለሚቱ አለባቸው በበኩላቸው "አርአያ ሊሆኑ የሚችሉና ሴቶችን ተጠቃሚ ያደረጉ የልማት ስራዎች ተመልክተናል" ብለዋል።

በዶሮ እርባታ፣ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በባዮ ጋዝና ሌሎች የተሰሩ ውጤታማ ስራዎችን ወደ ክልላቸው ወስደው በመተግበር አባላትን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

የፌዴራል ብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን የሚበልጡ አባላት እንዳሉት ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም