የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ማሻሻል ለአካባቢና ለደን ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው-ኮሚሽኑ

74

ጅማ፣ ታህሳስ 25/2013 (ኢዜአ) የአርሶ አደሩን የአኗኗር ዘይቤ ማሻሻል ለአካባቢና ለደን ጥበቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የከፋ ዞን የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ከጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ተራእዶ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የደን አጠባበቅና የኑሮ ማሻሻያ የአሰልጣኞች ስልጠና በጅማ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡


ለዞኑ የደን ሀብት ባለሙያዎች የተዘጋጀው ስልጠና አሳታፊ የደን አስተዳደር ስርዓት ማጎልበት፣ በቢዝነስ እቅድ አያያዝና በዘመናዊ የገንዘብ አስተዳደር ላይ ያተኮረ ነው።

የፌደራል የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ግርማ በወቅቱ እንደገለጹት አርሶ አደሩ ኑሮው ከተሻሻለና የሚፈልገውን ገቢ ማግኘት ከቻለ ደንን ከጥፋት የመታደግ አቅም ይኖረዋል።

"አርሶ አደሩ ኑሮው ከተሻሻለ ደንን ከጥፋት ይታደጋል እንጂ የጥፋቱ መንስኤ ሊሆን አይችልም" ብለዋል፡፡

አርሶ አደሩ ከደኑ እየተጠቀመ የደን ሀብት የሚጠብቅበትን አሰራር ለመዝርጋት ታስቦ ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል ።

የስልጠናው አስተባባሪና የከፋ ዞን የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጽህፈት ቤት ባለሙያ አቶ እያሱ ወልደጊዮርጊስ ስልጠናው በተጨማሪነት በጥምር የደን ልማት በሚከናወኑ ዘመናዊ የንብ ማነብና የቅመማ ቅመም ልማት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

"እንዲሁም የደን ሀብት ደህንነት በሚረጋገጥባቸው መንገዶች ላይ ያተኩራል" ብለዋል።

በስልጠናው ከቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የግብርና መምህራን ጋር ውይይትና የልምድ ልውውጥ እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም