ወንጀለኞችን ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን መሆናቸውን የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

84

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 25/2013( ኢዜአ) በመተከል ዞን በወገኖቻችን ላይ ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ግድያ የፈፀሙ ወንጀለኞችን ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን መሆናቸውን የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ኃይል በመተከል ዞን የዳንጉር ወረዳ አመራሮችና የተፈናቀሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወላጆች ጋር ተወያይቷል።

ግብረ ሃይሉ በታጣቂዎች ጥቃት ቤተሰቦቻቸውን ያጡ፣ ቤታቸውና ንብረታቸው ወድሞባቸው የተፈናቀሉ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላትን አወያይቷል።

በውይይቱም ተደራጅቶ ጥቃት ያደረሰው ሽፍታ ቡድን በርካታ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ ሌሎችንም ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ማጥቃቱን ገልጸዋል።

"በጥቃቱ በርካታ ቤተሰቦቻችንን አጥተናል፣ ንብረታችንን አጥተናል፣ ቤታችን ተቃጥሎብን አሁን በጣም ከባድ ችግር ላይ ነው የምንገኘው" ብለዋል።

በመሆኑም የጋራ ጠላታችን የሆነውን የታጠቀ ሃይል ለመያዝ ለሚደረገው ጥረት ሁሉ ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ነን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በግብረ ሃይሉ የሕግ ማስከበርና የፀጥታውን ዘርፍ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፤ የታጠቀውን ሃይል በማደን ለህግ ለማቅረብ የተጠናከረ ዘመቻ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ሂደት የአካባቢው ነዋሪ እያደረገ ያለውን ትብብር አድንቀው ወንጀለኞችን ለመያዝ በሚደረገው ጥረት ትብብሩን እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።

አሁን ላይ ወንጀለኞች መያዝ መጀመራቸውን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል አስራት በስጋት የሸሹ የአካባቢው ነዋሪዎች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ችግሩን ለመፍታት ከሃገር ሽማግሌዎች፣ ከነዋሪዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር የሚካሔደው የቅንጅት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሌተናል ጄኔራል አስራት አረጋግጠዋል።

ለተፈናቀሉ ዜጎች አስቸኳይ እርዳታ የማድረስ ስራው እንደሚቀጥል የተናገሩት ሌትናል ጀኔራሉ ለዚህም የፀጥታ አካሉ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር ስራ ይሰራል ብለዋል።

ግብረ ሃይሉ የዳንጉር ወረዳ አመራሮችንና ሕዝቡን የማረጋጋት ስራ በማከናወን ላይ ያሉ የመንግስት አካላትን በማወያየት እስካሁን ያከናወኗቸውን ተግባራትም ገምግሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም