"ግለሰብ፣ ቤተሰብ እና ኅብረተሰብ ላይ በመስራት ዘላቂ ሠላም ይረጋገጣል" - ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል

92

ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) የግለሰብ፣ የቤተሰብ እና የኅብረተሰብ አመለካከት ላይ በመስራት 'ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ ይቻላል' ሲሉ የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

የሠላም ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች አመራርና አባላት በቢሾፍቱ ስልጠና እየሰጠ ነው።

የሠላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የሠላም ግንባታ አቅጣጫ ተግባራት በመከታተልና በመደገፍ ረገድ የጎላ ድርሻ ነበረው።

መድረኩ ምክር ቤቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በአዋጅ ሲያቋቁም ጀምሮ የተሰጠውን ተልዕኮ ሲወጣ የቆየው እንዴት ነበር የሚለውን ለመፈተሽና በቀጣይ መስራት ስላሉብን ጉዳዮች ግብዓት ለመሰብሰብ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

የስልጠና መድረኩ የቋሚ ኮማቴ አመራርና አባላትን የቁጥጥር አቅም ማጎልበት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

ሠላም ከግለሰብ የሚጀምር ወደ አገር ከፍ ብሎ የሚታይ በመሆኑ "በግለሰብ፣ በቤተሰብና በማኅበረሰብ ሠላም ላይ በመስራት ነው ዘለቄታዊ ሠላም ማረጋገጥ የሚቻለው" ብለዋል ሚኒስትሯ።

በፀጥታ ኃይል የሚጠበቅ ሠላም ጊዜያዊ መሆኑን ገልጸው፤ ዘላቂነት ያለው ሠላም ለማረጋገጥ በመላው ኅብረተሰብ ላይ መስራት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

"የለውጡ አመራር እየተከለ ያለው የሠላም ግንባታ አቅጣጫ መዋቅራዊ በመሆኑ የሠላም ግንባታችን ተሰርቶ የሚጠናቀቅ ነው" ብለዋል ሚኒስትር ሙፈሪያት።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የስልጠና መድረክ ስነ-ልቦናዊ ውጥረትን በመቆጣጠር የስኬት ግስጋሴን ማፋጠን፣ የሠላም ፖሊሲና ስትራቴጂና ቀጣናዊ ጉዳዮች የሚሉትን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ምክክር ይደረጋል።

በተጨማሪም የሚኒስቴሩ የሁለት ዓመት አፈፃፀም፣ የሠላም ዘርፍ ፍኖተ ካርታና የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እንዲሁም የፖሊስ ኮሚሽን፣ የፋይናንስ ደህንነትና የመረጃ መረብ ደህንነት ሪፎርም ጉዳዮች እንደሚነሱም ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም