በኢንዱስትሪዎች በዝቅተኛ የደመወዝ ክፍያ የሚሰሩ ሴቶችና ወጣቶች ተጎጂ መሆናቸው ተገለጸ

83

አዳማ ታህሳስ 24/2013 (ኢዜአ) በኢንዱስትሪዎች ዝቅተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው የሚሰሩ ሴቶችና ወጣቶች በእጅጉ እየተጎዱ መሆናቸውን የሴቶች ፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በሶስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ባደረገው ጥናት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ መክሯል።

በሚኒስቴሩ የሴቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አህመድ እንደገለፁት መስሪያ ቤታቸው  በአዳማ፣ እስቴርን እና ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የመስክ ምልከታና ጥናት አድርጓል።

በዚህም ሴቶችና ወጣቶች በስፋት የስራ እድል ቢፈጠርላቸውም   በወር እያገኙ ያሉት ዝቅተኛ ክፍያ 750 ብር መሆኑን አመላክተዋል።

ወሩን ሙሉ ለፍተው የሚያገኙት ገንዘብ ለምግብና ቤት ኪራይ የሚበቃ አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ መንግስት ችግሩን ለመፍታት  ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን በ2011ዓ.ም የወጣው አዋጅ በፓርኮቹ አልተተገበረም ብለዋል።

መብታቸውን የሚጠይቁ ማህበራት በፓርኮቹ ያለመደራጀታቸው አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በርካታ ወጣቶችና ሴቶች ስራቸውን  ለቀው እንደሚሄዱ በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

የአዳማው የምክክር መድረክ ችግሩን ለመፍታት ከተወካዮች ምክር ቤት፣ በየደረጃው ከሚገኙ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች እንዲሁም አደረጃጀቶች ጋር በቅንጅት ለመስራት መሆኑንም ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ህፃናት ፣ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ  ወይዘሮ አበባ ዩሴፍ በበኩላቸው  በኢንዱስትሪ ፓርኮች በተደረገው የመስክ ምልከታ ለሠራተኞች እየተከፈለ ያለው ወርሃዊ ክፍያ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አረጋግጠናል ብለዋል።

ችግሩ ለመፍታት ሚኒስቴሩ  ያከናወነውን የጥናት ውጤት እኛም በመስክ ምልከታ አረጋግጠናል ያሉት ሰብሳቢዋ፣ በፓርኮቹ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ኢንዱስትሪዎችና አሰሪ ተቋማት በሚስተዋሉ ችግሮች ሴቶችና ወጣቶች እየተጎዱ መሆኑን ተናግረዋል።

አዋጁ በሁሉም የልማት ተቋማት ተፈፃሚ እንዲሆንና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ፣ የኢንዱስትሪዎች ሠላም፣ ደህንነትና ውጤታማነት እንዲረጋገጥ ዘላቂነት ያላቸውን ስራዎች እየተሰራ ነው ብለዋል።

ዝቅተኛ የክፍያ ወለል ለመወሰን የወጣው አዋጅ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሁሉም የኢንቬስትመንት ተቋማት ተፈፃሚ እንዲሆንና አተገባበሩን ለመከታተል ምክር ቤቱ ከባለደርሻ አካላት ጋር  እንደሚሰራ አስታወቀዋል።

ምክር ቤቱ የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ዘላቂ የሆነ ድጋፍና ክትትል ልያደርግልን ይገባል ያሉት ደግሞ በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ፍረህይወት ሃይሉ ናቸው።

ወጣቶችም ሆኑ ሴቶች ለእውቀታቸው፣ ጉልበታቸውና ለለፉበት ስራ ተገቢውን ክፍያ ማግኘት እንደሚገባቸው ጠቁመው ፣ ለዚህም አመቺ አሰራር ከመፍጠር ባለፈ የአዋጁን ተፈፃሚነት መከታታል ላይ ሁሉም ባለደርሻ አካላት በጋራ መስራት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም