የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ተጠናቀቀ

1753

አዲስ አበባ ታህሳስ 24 /2013 (ኢዜአ) የደርባ ሲሚንቶ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ዛሬ ተጠናቀቀ።

በዘንድሮው የቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ መከላከያ፣ ወላይታ ዲቻ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ባህርዳር ከነማ፣ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ፣ መደወላቡ ዩኒቨርሲቲና ሙገር ሲሚንቶ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው።

ከታህሳስ 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ስፖርት ሜዳና በሶዶ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ውድድር ዛሬ ተጠናቋል።

በዚሁ መሰረት በሊጉ አራተኛ ሣምንት መርሃ ግብር ሶስት ጨዋታዎች ተካሄደዋል።

ወላይታ ዲቻ ሙገር ሲሚንቶን፣ መከላከያ አዲስ አበባ ፖሊስን፣ ባህርዳር ከነማ ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን በተመሳሳይ በአራት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

ወላይታ ዲቻ የመጀመሪያውን ዙር ውድድር በስምንት ነጥብ በመሪነት ሲያጠናቅቅ ሙገር ሲሚንቶና መከላከያ በተመሳሳይ ሰባት ነጥብ በጨዋታ ዙሮች ባሸነፉበት የውጤት ልዩነት በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ በሁለት ነጥብ የመጨረሻውን ሰባተኛ ደረጃ ይዟል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ የዘንድሮው የፕሪሚየር ሊጉ ውድድር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር፣ ለስፖርታዊ ውድድሮች በወጣው ፕሮቶኮል መሰረት ጨዋታዎች የሚካሄዱት ያለተመልካች መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በውድድሩ የሚሳተፉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞችና ሌሎች ባለሙያዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸው ወደ ውድድር መግባታቸውንም አመልክተዋል።

በመጀመሪያው ዙር ውድድር ክለቦች ተመጣጣኝ የሚባል ፉክክር እንዳደረጉና በስፖርታዊ ጨዋነት ረገድም መልካም የሚባል ነገር መታየቱን ተናግረዋል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች “በጀት የለኝም” በማለቱ ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ አለመሳተፉን አቶ ተክሉ ገልፀዋል።

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለውድድሩ ተሳታፊዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ በማድረግና ለተሳታፊዎች ላደረገው አቀባባልም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽንና የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቮሊቦል ስፖርት በጋራ መስራት የሚያስችላቸው የጋራ መግባቢያ ሰነድ በቅርቡ እንደሚፈራረሙም ጠቁመዋል።

በስምምነቱ አማካኝነት በወላይታ ሶዶ ከተማ የቮሊቦል ፕሮጀክት ማሰልጠኛ ማዕከል እንደሚከፈት ነው የተናገሩት።

የሁለተኛው ዙር የፕሪሚየር ሊግ ውድድር ከአንድ ወር እረፍት በኋላ በባሌ ሮቤ ከተማ እንደሚካሄድ ገልፀዋል።

የዘንድሮውን ፕሪሚየር ሊግ የደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ ስፖንሰር ማድረጉንና ቮሊቦል ፌዴሬሽኑ ከፋብሪካው ጋር የሚያቆየውን የአንድ ዓመት የስፖንሰርሺፕ ስምምነት መፈራረሙንም አክለዋል።

የ2012 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሩ ያለ አሸናፊ መሰረዙ የሚታወስ ነው።

ወላይታ ዲቻ ፕሪሚየር ሊጉን ስድስት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን የያዘ ሲሆን ሙገር ሲሚንቶ አንድ ጊዜ የሊጉ አሸናፊ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።