የአመራር ሳይንስና ጥበብ የተሰኘ መጽሐፍ ተመረቀ

333
አዲስ አበባ ሀምሌ 14/2010 በቀድሞው የጦር መኮንን ኮሎኔል ፈቃደ ገብረየስ የተጻፈ 'የአመራር ሳይንስ እና ጥበብ' የተሰኘ መጽሐፍ ዛሬ ተመረቀ። ደራሲው ኮሎኔል ፈቃደ፤ በእንግሊዙ ኦፕን ዩኒቨርሰቲ በስትራቴጂክ ሥራ አመራር የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በቀድሞዋ ሶቪዬት ሕብረት በወታደራዊ ሳይንስ የሁለተኛ ዲግሪ ማግኘታቸው ተገልጿል። በምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት/ኢጋድ/ በሚደረገው የደቡብ ሱዳን ግጭት አፈታት ላይ በታዛቢነት ማገልገላቸውና በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በአማካሪነት መስራታቸውም ተጠቅሷል። አገራቸውን ለ30 ዓመታት በወታደራዊ አገልግሎት ማገልገላቸው የተገለጸላቸው ደራሲው፤ ከዚህ በፊት 'ስትራቴጂክ' እና 'ድርጅታዊ የጤንነት ምርመራ' የተሰኙ መጽሐፍት ማሳተማቸው ተወስቷል። ለሦስተኛ ጊዜ ያሳተሙት 'የአመራር ሳይንስ እና ጥበብ' የተሰኘው መጽሐፋቸውም የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ታዋቂ የጥበብ ሰዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል። መጽሐፉን ለማዘጋጀት አራት ዓመታት እንደፈጀባቸው የገለጹት ኮሎኔሉ፣ በሕይወት ጉዟቸው ያካበቱትን ልምድ፣ ክህሎትና ዕውቀት ለማኅበረሰቡ ለማድረስና ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ በማለም እንደሆነ ተናግረዋል። አመራርነት "ከታናናሽ ተቋማት አስተዳዳሪዎች እስከ ታላላቅ የአገር መሪዎች ጥበብ ይፈልጋል" ያሉት ጸሃፊው "አመራርነት ጥበብ ብቻ ሳይሆን ሳይንስም ነው" ብለዋል። መጽሐፉ በሁለት ክፍሎች የተከፈ ሲሆን የመጀመሪያው ክፍል ጥልቅ ጥናት የተደረገባቸው የአመራርነት ጽንሰ-ሐሳቦች ሲሆን በሁለተኛ ክፍል ደግሞ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች የነበሩ የአገር መሪዎች፣ የጦር መኮንኖችና ታዋቂ ግለሰቦች የአመራርነት ታሪኮች የተካተቱበት ነው። መጽሐፉ ከሥነ-ጽሑፍ ቅርጽ ይልቅ በይዘት ላይ ትኩረት የሰጠ መሆኑን ጸሃፊው አመልክተዋል። 704 ገጾች ያሉት መጽሐፉ በ300 ብር ለገበያ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም