ለመንገድ ደህንነት የሚያግዙ የ40 ረዳሮች ተከላና ከ20ሺህ በላይ የፍጥነት መገደቢያ መገጠማቸው ተገለጸ

106

አዳማ ታህሳስ 24/2013( ኢዜአ) በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የ40 ራዳሮች ተከላና ከ20ሺህ በላይ ፍጥነት መገደቢያዎች ተሽከርካሪዎች ላይ መገጠማቸውን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሰልጣን ገለጸ።

ባለስልጣኑ የበጀት ዓመቱ አጋማሽ እቅድ አፈጻጸም ከፌዴራልና ክልሎች የዘርፉ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ እየገመገመ ነው።

በግምገማው መድረክ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት የትራንስፖርት ዘርፉ  በማዘመን የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል።

በተለይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የተሽከርካሪ አደጋን ከመቀነስ አንጻር ክልሎች፣ ተጠሪ ተቋማትና ባለስልጣኑ  በቅንጅት የመስራቱ ሁኔታ መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

በተለይ ቴክኖሎጅን ከመጠቀም አኳያ የፍጥነት መቆጣጠሪያ 40 ራዳሮች መትከል፣ ከ20ሺህ በላይ በሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ የመግጠም፣ የአልኮል መጠን ልየታና የደህንነት ቀበቶን መታጠቅ የሚያስገድድ መመሪያዎች ጭምር በማውጣት ወደ ተግባር የገባንበት ነው ብለዋል።

የህግ ማዕቀፎችን ከማሻሻልና ትራንስፖርት አገልግሎትን ዘመናዊ ከማድረግ አንፃር በተለይ ክልሎች ላይ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ የህዝብ መናኽሪያ እየተመቻቹ መሆናቸውን አቶ አብዲሳ አመልክተዋል።

የትራንስፖርት ዘርፉ በማዘመን  የመንገድ ድህንነትን ለማረጋገጥ ባለፉት ስድስት ወራት አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ደግሞ  በባለስልጣኑ የመንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ማስጨበጫ ዳይሬክተር አቶ ዮሐንስ ለማ ናቸው። 

የተሽከርካሪ አደጋን ለመከላከል  በተለያዩ ከተሞችና ዋና ዋና የማሳለጫ መንገዶች ተሳፋሪዎች ጭምር የደህንነት ቀበቶ መታጠቅ የሚያስግድድ መመሪያ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን  ተናግረዋል።

የአዳማው መድረክ በቀጣይ ስድስት ወራት መመሪያው በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች  ተፈፃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ የጋራ አቅጣጫ የሚቀመጥበት ጭምር መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

በዚህም የተቀናጀ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎችና የትራፊክ ፖሊሶች ስራ ወሳኝ ነው ያሉት አቶ ዮሐንስ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ተገቢውን እውቅት፣ ክህሎትና ስነ ምግባር የተላበሱ አሽከርካሪዎችን እንዲያፈሩ ለማስቻል በየደረጃው ካሉት ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም